ወ/ሮ ገነት ስለሺ የፎቶግራፍ ባለሞያ ስትሆን ነዋሪነቷ በአሜሪካ ሃገር ነው፡፡ በዓመታት ከሃገር ውጪ ቆይታዋ ያጋጠማት የጸጉር መርገፍ፣ መጎዳት እና ተስማሚ የሆነ የጸጉር ምርት ማጣት ችግር 'ሹሩባ የጸጉር ቅቤ' የተሰኘ ከላም ወተት የተመረተ የጸጉር ቅቤ ማምረቻ ተቋም እንድትከፍት እና ለዘመናት የቆየው የኢትዮጵያዊያን ጸጉርን ቅቤ የመቀባት ባህል ከኢትዮጵያ ውጪም እንዲስፋፋ ማድረግ እንድትችል አድርጓታል፡፡
ከላም ወተት የተመረትውን እና 'ሹሩባ ጸጉር ቅቤ' ስትል የሰየመችውን ምርትም የአፍሪካ ሃገራት እና በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ሱቆች እየሸጠች ትገኛለች፡፡ በቀጣይም ምርቷን በማስፋፋት በጸጉር ሳሙና/ሻምፑ፣ ኮንዲሽነር እና ሌሎችም ምርቶችን ለማዘጋጅት እቅድ እንዳላት ትናገራለች፡፡ ገነት በዩናይትድ ስቴትስ ጥቁር፣ ሴት እና ስደተኛ ሆኖ እየኖሩ የራስ የሆነ ተቋም መመስረት ስላለው ፈተናም አጋርታለች፡፡