“ትግራይ ውስጥ እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ካለፈው ሰኔ ወር ወዲህ የረድዔት ተደራሽነት እየተሻሻለ ቢሆንም የሰብዓዊ ረድዔት አጋሮቻችን እንደሚነግሩን ወደ ክልሉ የመግባት እና የመውጣት እንቅስቃሴው አሁንም የተገደበ ነው” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ቃል አቀባይ ገለጹ። ይህ መሆኑ ደግሞ የዕርዳታ አቅርቦቶች ለማስገባት እና የርዳታ ሥራው እንዲቀጥል ሠራተኞች ለማንቀሳቀስ አዳጋች ያደርግባቸዋል ብለዋል።
በሌላ በኩል ከአሁን ቀደም ለመድረስ አስቸጋሪ ወደነበሩት አካባቢዎች በአሁን ወቅት መድረስ መቻሉን የመንግስታቱ ድርጅት ምክትል ቃል አቀባዩ ፋርሃን ሃክ ተናግረዋል። ርዳታ ከሚያስፈልጋቸው 5.2 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 4 ሚሊዮኑ (ማለትም ሰባ አምስት ከመቶው) ያሉባቸው አካባቢዎች ባሁኑ ወቅት የሰብዓዊ ረድዔት እንቅስቃሴ መድረስ የሚቻል መሆኑን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ ባለፈው ግንቦት ወር ግን ለመድረስ የሚቻለው ሰላሳ ከመቶውን ብቻ ነበር ብለዋል።
አክለውም የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃክ በመኪና ርዳት ማጓጓዝ የሚቻለው በክልል እና በፌዴራል መንግሥት ከባድ ቁጥጥር በሚድረግበት በአፋር ክልል በኩል ብቻ በመሆኑ ክልሉ ውስጥ ያለው የርዳታ አቅርቦት በፍጥነት እያለቀ ነው ብለዋል። ከሁለት ሳምን ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዘ ባለፈው ሳምንት የርዳታ አቅርቦቶች የጫኑ ሃምሳ አራት መኪናዎች መቀሌ እንደደረሱ ያስታወሱት ፋርሃን ሃክ፤ ያ በቂ ስላልሆነ በየቀኑ ከዚያ በላይ ርዳታ የያዙ ተሽከርካሪዎች መድረስ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ከሰጠ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ረድዔት በረራ አገልግሎት ባለፈው ቅዳሜ ወደትግራይ የተሳካ የሙከራ በረራ ማደረጉን ገልጸው መደበኛ በረራዎች ከነገ ጀምሮ እንደሚቀጥል ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
አያያዘውም “በክልሉ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ እንዳይባባስ መሰረታዊ አገልግሎቶች፤ የኤሌትሪክ፣ የመገናኛ የባንክ አገልግሎቶች እንዲሁም መደበኛ በረራዎች እንዲቀጠሉ ጥሪ ማሰማታችንን እናቀጥላለን፥ አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍም ያስፈልጋል” ብለዋል። “እስከዚህ የአውሮፓ 2021 ዓ.ም ማብቂያ ባለው ጊዜ ለትግራይ ሰብዓዊ ረድኤት ከሚያስፈልገው አጠቃላይ ወጪ ከግማሽ በላዩን የሚይዘው ከ430 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ እንዲሰጠን አሁንም መጠየቃችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።
(መረጃው ከመንግሥታቱ ድርጅት ምክትል ቃል አቀባይ የዛሬ ዕለታዊ መደበኛ ገለጻ የተገኘ ነው)