የፓርኪንሰን ሕሙማን ድጋፍ ማኅበር በኢትዮጵያ ከተመሰረተ አስራ ሁለት ዓመት ይሆነዋል፡፡ የድርጅቱ መስራች ክብራ ከበደ ትሰኛለች፡፡ ክብራ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት የፓርኪንሰን በሽታ ሲይዛት በሽታሽ ይሄ ነው የሚለኝ ባለመኖሩ ብዙ ተጨንቄ እና ተጉላልቼ ነበር ትላለች፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላም ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ውጪ ሃገር ሄዳ ሕመመሽ ፓርኪንሰንስ ነው ስትባልም የችግሯን ግማሽ መረዳቷ ደስተኛ እንዳደረጋትም ትገልጻለች፡፡
በኢትዮጵያም የህመም ማስታገሻ እንጂ ፈዋሽ መድሃኒት በሌለው ፓርኪንሰንስ ችግር ብዙዎች ቢጠቁም በበሽታው ዙሪያ ግን ምንም ኝዛቤ አለመኖሩ ማኅበሩን እንድትከፍት ገፋፋት፡፡ የፓርኪንሰን ማኅበሩ ከተመሰረተ ጀምሮም በበሽታው ዙሪያ ግንዛቤን ለመፍጠር የእግር ጉዞዎች፣ የውይይት ምሽቶች፣ የምክር አገልግሎቶች፣ እና ለጀማሪ የህክምና ባለሞያዎችም ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን ሕሙማኑም የምክር፣ የገንዘብ እና የመድሃኒት ድጋፍ እንዲያገኙ በማመቻቸት እየሰራ ይገኛል፡፡ ይሁንና ክብራ ስራቸውን ለማስፋት ኮቪድ 19 ጨምሮ እጅግ ብዙ ጋሬጣዎች እያጋጠሟቸው እንደሆነ ለአሜሪካ ድምጽ ገልጻለች፡፡