በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የምግብ ዋጋ ግሽበት ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን ያሰጋል


የምግብ ዋጋ ግሽበት ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን ያሰጋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:18 0:00

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የምግብ ዋጋ ንረት ለማረጋጋት መንግስት መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች በፍራንኮ ቫሉታ እንዲገቡ ማድረጉ በህብረተስቡ ዘንድ የሚታየውን የኑሮ ውድነት እንዳላቃለለ፣ የምግብ ዋጋም ከበፊቱ ይበልጥ እየጨመረ እንደሄደ ሸማቾች ይናገራሉ። ፍራንኮ ቫሉታ ብቻውን የዋጋ ንረቱን አያስተካክልም የሚሉት የምጣኔ ሀብት ተንታኞችም በኢኮኖሚውና በፓለቲካው ዙሪያ አስቸኳይ ማሻሻያዎች ካልተደረጉ ግሽበቱ መመለስ ወደማይቻልበት ደረጃ ሊደርስ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚያገኙት ገቢ በተለይ ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን በበቂ ሁኔታ ለመግዛት አዳጋች እየሆነባቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ በምሬት ይገልፃሉ፣ ምክንያቱ ደግሞ የማያቋርጥ የዋጋ ጭማሪ ነው።

ቀደም ሲል የሰማችኃት ሰብለወርቅ ያዛቸው ትባላለች። የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ስትሆን በተሰማራችበት አነስተኛ ንግድ በምታገኘው ገቢ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም እንዳቃታት ትገልፃለች። መንግስት ዋጋ ለማረጋጋት የሚያደርገው ጥረትም ነጋዴዎችን ምርት እንዲይዙ እንደሚያደርጋቸውና ለበለጠ ለእጥረትና ዋጋ ጭማሪ ከመዳረግ ውጪ ለውጥ እንደማያመጣ በምሬት ትናገራለች።

የምግብ አቅርቦት ከሀገር ምርት እና ምርታማነት፣ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጨምረው የህዝብ ቁጥር፣ ከውጪ ገዝቶ ከማከማቸትና ከውጪ ምርዛሬ አቅም ጋር ግንኙነት አለው። ታዲያ ይሄ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ከየት መጣ? የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ለሆኑት ዋሲሁን በላይ ያቀረብንላቸው ጥያቄ ነበር።

በኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ የሄደው የፖለቲካ አለመረጋጋትና ተደጋጋሚ ግጭት ደግሞ ማምረት የሚችሉ ዜጎች እንዳያመርቱና በተቃራኒው ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲፈልጉ ማድረጉም ለዋጋ ግሽበቱ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሆነ አቶ ዋሲሁን ያብራራሉ።

በኢትዮጵያ በየጊዜ እየናረ የሚሄደውን የምግብ ዋጋ ለማረጋጋት የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያዚያ ወር ላይ የፍራንኮ ቫሉታ ወይም ምርትን ያለውጭ ምንዛሬ ፈቃድ ለስድስት ወር ማስገባት እንዲቻል ፈቅዶ ነበር። ፍራንኮ ቫሉታ ምን ማለት ነው? እንዴትስ ነው ገበያ የሚያረጋጋው? ለአቶ ዋሲሁን ያነሳሁት ሌላ ጥያቄ ነው።

መንግስት ይህን ፈቃድ ከሰጠ በኃላ በርካታ አስመጪዎች እንደ ዘይት፣ ሩዝ እና የህፃናት ምግብ የመሳሰሉ ምርቶችን በብዛት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባታቸው ቢገለፅም ይህ የፖሊሲ ለውጥ ግን በምርት አቅርቦትና በዋጋ ላይ ግን ምንም መሻሻል አላሳየም። ሰብለ እንደምትለው እንደውም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የምግብ ዋጋ የበለጠ ጨምሯል።

የፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ በትክክል ያመጣውን ለውጥ ለማወቅ ገና ጥናት መካሄድ ቢኖርበትም፣ በገበያ ላይ የዋጋ ለውጥ ላለማምጣቱ ግን በርካታ ተያያዥ ምክንያቶች እንዳሉት አቶ ዋሲሁን ያስረዳሉ። በዋናነት ግን መንግስት ጎን ለጎን መስራት የነበረትን ተመጋጋቢ የዋጋ ማረጋጊያ ስራዎችን አለመስራቱ ነው።

በኢትዮጵያ በከፍተኛ መጠን ላይ የደረሰውን የምግብና ሌሎች ሸቀጦች ግሽበት ለማረጋጋትና ህብረተሰቡን ከገባባት ከፍተኛ የኑሮ ውድነት አጣብቂኝ ለማላቀቅ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው በተለይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መሰረት ያደረገበት የግብርና ምርት እንዲጨምር ማድረግ፣ የግብርና ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ በማቅረብና የተፈናቀሉ ገበሬዎች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው ምርታማ እንዲሆን ማድረግ መሰረታዊ እርምጃ መሆኑን አቶ ዋሲሁን ያስረዳሉ።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ የሚሄድ የአየር ንብረት ለውጥ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚከሰቱ ግጭቶች በዓለም ደረጃ የምግብ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል። ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሸማች ሀገራት ተጨማሪ ጫና ይፈጥራል። በመሆኑም የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ማሳደግ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጠቁመዋል።

XS
SM
MD
LG