ስድስተኛውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ በተመለከተ በኢትዮጵያ ተቀማጭ የአውሮፓ ህብረት ልዑካን እንዲሁም የአስራ ሁለት ሃገሮች ኤምባሲዎች መግለጫ አውጥተዋል።
ረጅም ጊዜ ያስቆጠርን የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አጋሮች እንደመሆናችን ኢትዮጵያ ብዛት ያለው ስብጥር ያለው ህዝቧ ሙሉ በሙሉ የሚሳተፍበት ይበልጡን ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲኖራት እንደግፋለን ብለዋል።
ምርጫዎችን በሚመለከቱ ህግጋት ረገድ ታላላቅ እርምጃዎች ተመዝግበዋል፤ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ሲቪል ማኅበራትን እንዲሁም መገናኛ ብዙሃንን ባሳተፈ መልኩ የምርጫው ሂደት ተዓማኒ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ አከናውኗል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኦስትሪያ፣ የአውስትሬሊያ፣ የካናዳ፣ የዴንማርክ፣ የጀርመን፣ የአይርላንድ፣ የጃፓን፣ ለክሰምበርግ፣ ኒው ዚላንድ፣ ኖርዌይ፣ ኔዘርላንድ እና ዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ልዑካን በመግለጫቸው የምርጫው ሂደት አያሌ የአፈጻጸም ችግሮች የተስተዋሉበት እንደነበርም አመልክተዋል።
ምርጫው የተከናወነው ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በእስር ላይ በሚገኙበት፣ የመገናኛ ብዙሃን አባላት በሚዋከቡበት፣ ፓርቲዎች በነጻነት የምረጡን ቅስቀሳ ለማካሄድ በተቸገሩበት አስቸጋሪ ድባብ ውስጥ እንደነበር የኤምባሲዎቹ መግለጫ አትቷል።
ብዛት ባላቸው አካባቢዎች የጸጥታ ችግር መኖሩን ተፈናቃዮች ድምጽ ለመስጠት እንዲመዘገቡና በበቂ ሁኔታ በምርጫው እንዲካፈሉ ያልተደረገበት ካለፉት ሦስት ሃገራዊ ምርጫዎች ጋር ሲነጻጸር የሴት ዕጩዎች ቁጥር በአንድ ሶስተኛ የቀነሰ መሆኑን አመልክተዋል።
ምርጫ ብቻውን የዲሞክራሲ ሽግግር ሊያመጣ ወይም የተደቀኑት የፖለቲካ ተግዳሮቶች መፍትሄ ሊሰጥ አይችልም ያሉት ኤምባሲዎቹና የአውሮፓ ህብረት ልዑካን የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሁሉም ባለድርሻዎች ስፋት ያለው ብሄራዊ ውይይት ሂደት ለመጀመር እና ላሉት ተግዳሮቶች ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት ቁርጠኛ እንዲሆኑ እንማጸናለን ብለዋል።
ይህ መሆኑ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲያብብ፣ በሀገሪቱ ዙሪያ ግጭቶች እንዲወገዱ እና ለትግራይ ሁኔታም ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲገኝ ለማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።