በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዘመናዊት የዛምቢያ መስራች አባት ኬኔት ካውንዳ አረፉ


የዛምቢያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኬኔት ካውንዳ
የዛምቢያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኬኔት ካውንዳ

የዛምቢያ መስራች አባት በመባል የሚታወቁት ኬኔት ካውንዳ በዘጠና ሰባት ዓመታቸው በሞት ተለይተዋል።

ካውንዳ ሃገሮቻቸውን በአፍሪካ የሁከት እና የድል ታሪክ በተመዘገቡባቸው ወቅቶች ህዝቦቻቻቸውን መርተው ካለፉ የነጻነት ትግል መሪዎች አንዱ ናቸው።

ሃገራቸው ዛምቢያ እአአ በ1964 ከብሪታንያ ቅኝ ግዛትነት ስትወጣ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ሆነው እስከ 1991 ሥልጣን ላይ ቆይተዋል።

ካውንዳ ትናንት ሃሙስ ከቀትር በኋላ እንዳረፉ የዛምቢያ መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን ከጥቂት ቀናት በፊት በሳምባ ምች ህመም ምክንያት ዋና ከተማዋ ሉሳካ የሚገኝ ሆስፒታል ገብተው ሲታከሙ እንደነበር ረዳቶቻቸው ገልጸዋል።

የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጋ "ተወዳጁ የሀገራችን መስራች አባት" ሲሉ ለገለጹዋቸው መሪ የሃያ አንድ ቀን የብሂራዊ ሃዘን ጊዜ አውጀዋል።

ለአፍሪካ አንድነት ተሟጋቾች ጥምረት የሚባል ህብረት መስራች የሆኑት ጋናዊ ጠበቃ ሳራፎ አብረብሬሴ የኬኔት ካውንዳ ተደማጭነት በዛምቢያ ግዛት ውስጥ ብቻ የተገደበ እንዳልነበረ ይናገራሉ።

"ኬኔት ካውንዳም ጸረ ቅኝ እገዛዝ ትግላቸውን በመቀጠል ኔልሰን ማንዴላን፣ ሮበርት ሙጋቤን እና ሳም ኑዮማን ለመሳሰሉት መሪዎች ክዋሜ ንክሩማ በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ እንዳደረጉት ሁሉ በደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል የአመራር ሚና ሲጫወቱ ኖረዋል፥ ታሪካቸው ተጽፎ ለዘላለም ይኖራል" ብለዋል።

በጆሃንስበርግ ዩኒቨርስቲ መምህሩ ኢማኑኤል ማታምቦ በበኩላቸው ብዛት ያላቸው ቋንቋዎች እና ብሄረሰቦች ባሏት ሃገር እኩልነት የሰፈነባት ዘመናዊት ዛምቢያን ራዕያቸው አድርገው የኖሩ ሲሉ ይገልጹዋቸዋል። የዘወትር መፈክራቸው "አንድ ዛምቢያ፣ አንድ ሃገር" ‘ዋን ዛምቢያ፣ ዋን ኔሽን" የነበረው ኬኔት ካውንዳ እጅግ የተለያዩ ቋንቋዎች እና ብሄረሰቦች ያቀፈችው ሃገር እንድነቱዋ ጸንቶ እንዲኖር አድርገዋል" ብለዋል። ይህ ደግሞ ለዛምቢያ ብቻ ሳይሆን ለመላዋ አፍሪካ ታላቅ ክንዋኔ ሆኖ የሚመዘገብ ነው ሲሉም ፕሮፌሰሩ ለቪኦኤ ገልጸዋል።

እአአ በ1924 ከሚሲዮናውያን ከአጎራባች ማላዊ ከሆኑ ሚሲዮናውያን መምህራን የተወለዱት ካውንዳ እንደሌሎች የድህረ ነጻነት የአፍሪካ መሪዎች ጉዋዶቻቸው እንደታንዛኒያው ጁሊየስ ኒየሬሬ እና የዚምባቡዌው ሮበርት ሙጋቤ ሁሉ የስራ ህይወታቸውን በመምህርነት ከጀመሩ በኋላ እንዳመሩ የህይወት ታሪካቸው ያወሳል።

XS
SM
MD
LG