በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ 100 ግድቦችን እገነባለሁ ማለቷ ግብፅን አስቆጥቷል


ኢትዮጵያ 100 ግድቦችን እገነባለሁ ማለቷ ግብፅን አስቆጥቷል
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:30 0:00

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ በመጪው አመት እስከ 100 የሚደርሱ አነስተኛና መሀከለኛ ግድቦችን እገነባለሁ ማለታቸውን ተቃውመው የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ትላንት መግለጫ አውጥተዋል። የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህጎችን እስካከበረች ድረስ የተፈጥሮ ሀብቷን መጠቀም ትችላለች ማለታቸውን ፋና ብሮድካቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።

የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አህመድ ሀፌዝ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ በመጪው አመት በሀገሪቱ በሚገኙ የውሃ አካላት ላይ አንድ መቶ ትናንሽ እና መሀከለኛ መጠን ያላቸው ግድቦችን ለመገንባት ያላቸውን እቅድ መናገራቸውን ነቅፈው ያወጡትን ቁጣ ያዘለ መግለጫ አንድ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን አስተላልፏል።

ሀፌዝ በመግለጫቸው ይህ እቅድ ግብፅ እና ሱዳንን ባስቆጣው የህዳሴ ግድብ አሞላል ዙሪያ ባለው ግጭት የኢትዮጵያን ቀና ያልሆነ አመለካከት ያሳያል ካሉ በኃላ ኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት እቅድ ሲኖራት ጎረቤቶቿ ላይ ጉዳት ከማድረሷ በፊት ልትማከር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲን በጉዳዩ ላይ በስልክ ለማናገር ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው ባይሳካም፣ በሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ስለጉዳይ ተጠይቀው፣ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ህጎችን እስካከበረች ድረስ፣ በተለይም ድምበር ተሻጋሪ ወንዞችን አጠቃቀም ህግ እስካከበረች ድረስ የትኛውንም ሀብት የመጠቀም መብታችን እንደተጠበቀ ነው ማለታቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።

ፋና በዘገባው፣ አምባሳደር ዲና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አንዲት የተፈጥሮ ሀብቷን በራሷ መጠቀም ከምትችል ሉዓላዊት ሀገር የሚጠበቅ ሀሳብ ነው ማለታቸውንም ጨምሮ ጠቅሷል።

የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ ባለፈው ሳምንት ጅቡቲን በጎበኙበት ወቅት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የግድቡን ሙሌት አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ጋር ከገቡበት አለመግባባት ለመውጣት በድርድር ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ላይ የመድረስ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረው ነበር።

"የህዳሴ ግድብ ሁኔታ የአጠቃላይ ቀጠናውን ጥቅም የሚነካ ነው። እናም በአሞላሉና አፈፃፀሙ ላይ ተገቢ እና ሚዛናዊ ስምምነት ላይ በአስቸኳይ መድረስ አለብን። የሌሎችን ሀገራት ጥቅምና መብት ሳያስጠብቅ የራሱን እቅድ ለማስፈፀም የሚሞክር ማንኛውንም አካል ግብፅ ትቃወማለች።"

በግብፅ የፖለቲካ ሶሲዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ሰኢድ ሳዴክ ለአሜሪካ ድምፅ ሲያስረዱ ኢትዮጵያ በሐምሌ ወር ሁለተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ ሙሌት የማካሄዷ ጉዳይ የግብፅን ህዝብ አስቆጥቷል ይላሉ።

"የህዝቡ አስተያየት ቁጣ የተሞላበት ነው እና ሁሌም የግብፅን ህዝብና መንግስት በመተንኮስ ለሚናገሩት የኢትዮጵያ ፓለቲከኞችና ሚዲያ ትንኮሳ መንግስት ምላሽ እንዲሰጥ እየገፋፉት ነው። "

ሳዴክ በተለይ ከግብፅ ውጪ የሚገኙ የግብፅ ተቃዋሚ ሀይሎች መንግስት ግጭቱን በአግባቡ እያስተናገደ አይደለም በማለት የተቃውሞ ሰልፍ እየጠሩ መሆኑንም ተናግረዋል። አክለውም የግብፅ ባለስልጣናት በተለይ እንደ አውሮፓ ህብረት፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪካ ህብረት ያሉ ሀያላን አደራዳሪዎች ተፅእኗቸውን ተጠቅመው ለምን ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለማምጣት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ግራ መጋባታቸውን ያስረዳሉ።

የአሜሪካ ድምፅ ያናገራቸው፣ በዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ክፍለ ግዛት በሚገኘው ብሄራዊ መከላከያ ዩንቨርስቲ መምህር የሆኑት ፓውል ሱሊቫን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን መገንባቷ በራሱ ቁጣ የሚያጭር ሆኖ ሳለ 100 መቶ ግድቦችን እገነባለሁ ማለቷ የበለጠ ፀቡን የሚያጋግል መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ ግብፅ ምላሽ መስጠቷ አይቀርም የሚሉት ሱሊቫን ኢትዮጵያ ሰላም የምትፈልግ ከሆነ እያደረገች ያለችው ግን ተቃራኒውን ነው ሲሉ ያስረዳሉ። ወደ ጦርነት ከተጋባ ሁሉም ወገን ከፍተኛ ኪሳራ ይደርስበታል የሚሉት ሲሊቫን ምክንያታዊ ወደ ሆነ ስምምነት መድረስ ባይቻል እንኳን አሁን ባለው ሁኔታ ነገሮች ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ እየሄዱ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የግብፅ እና የሱዳን ወታደሮች በጋራ የጀመሩትን ስድስት ቀን የፈጀ የመሬት፣ የአየር እና የባህር የጦር ልምምድ በዚህ ሳምንት ማጠናቀቃቸውን አሶሽዬትድ ፕሬስ ዘግቧል። ይህ ልምምድ ሁለቱ ጎረቤት ሀገሮች የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትስስር ማጠናከራቸውንና ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ውጥረት እየተባባሰ ባለበት ሁኔታ ሀይል እንደሚያሳይ ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።

የጋራ የጦር ልምምዱ ሰኞ እለት ካርቱም አጠገብ በሚገኝ የጦር ሰፈር ሲጠናቀቅም የሁለቱ ሀገራት ልዩ አማካሪ የሆኑት የሱዳኑ መሀመድ ኦትማን አልሁሴን እና የግብፁ አቻቸው ሌተናል ጀነራል መሃመድ ፋሪድ መገኘታቸውን የኤፒ ዘገባ ያመለክታል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው ባይሳካም፣ ምላሻቸውን እንዳገኘን ይዘን እንመለሳለን።

XS
SM
MD
LG