በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ቀውስ ፡የዮናይትድ ስቴትስ ስትራቴጂና ፖሊሲ ምላሽ


ከግራ ወደቀኝ ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ ፣ የተከበሩ ሮበርት ኤፍ ጎዴክ፣ ሚስ ሳራ ቻርለስ

የዮናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሜቴ ሀሙስ ግንቦት 19/2021 “ የኢትዮጵያ ቀውስ ፦የዮናይትድ ስቴትስ ስትራቴጂ እና የፖሊሲ ምላሽ ” በሚል ርዕስ ስብሰባ አከናውኗል።በዚህ የባለስልጣናትን ምስክርነት እና ማስገንዘቢያ ባስተናገደው መድረክ ላይ በትግራይ ክልል ውስጥ እየደረሱ ናቸው የተባሉ ሰብዓዊ ወንጀሎች ተዘርዝረዋል። ዩናይትድ ስቴትስ በመውሰድ ላይ ያለቻቸው ፖለቲካዊ እና ሰብዓዊ ምላሾችም ተሰምተዋል። ሀብታሙ ስዩም የስብሰባውን ዐበይት ነጥቦች በቀጣይ ዘገባው ያስቃኘናል።

የኮሚቴው ሊቀመንበር ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር ለበርካታ ዓመታት የዮናይትድ ስቴትስ ስትራቴጂካዊ አጋር ሆና በቆየችው ኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ውስጥ የተፈጠረው ከስተት ዳርፉርን በመሰሉ ዘግናኝ ሰብዓዊ ጥፋቶችን ያስተናገዱ ስፍራዎችን ሁነት የሚያስታስ እንደሆነ ጠቁመዋል ሁሉን የጦርነቱን ተዋናዮች በመብት ጥሰት ከሰዋል።

“ ሁሉም ወገኖች በመብት ረገጣ ጉዳይ ጥፋተኛ ናቸው።ሆኖም ተበታትነው ያገኘናቸው ማስገንዘቢያዎች የሚጠቁሙት የኢትዮጵያ ፣ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት አባላት እና አጋር ሚሊሺያዎች ከሌሎች ጋር ሊነጻጸር የማይችል ፣ግዴለሽነት እና ክፋት በተሞላበት መልኩ ሰላማዊ ሰዎችን በማጥቃት ረገድ ኃላፊነቱን ይወስዳሉ።የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ የተቃጣ ወንጀል እየተመለከትን ነው ” ብለዋል።

በዚህ ስብሰባ ላይ በትግራይ ክልል ያለውን ሁሉን አቀፍ ችግር ለማስረዳት ከቀረቡት ባለስልጣናት መካከል አንዱ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ተጠባባቂ ረዳት ጸሃፊ የሆኑት የተከበሩ ሮበርት ኤፍ ጎዴክ ናቸው ። እሳቸው ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ሁነት አሰቃቂነት ሲያስረዱ ፣

“ በትግራይ ያለው ጥቃት አሰቃቂ ነው። ህሊናን የሚበጠብጥም ነው።ግጭቱ በህዳር ወር ከጀመረ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲሞቱ ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቆስለዋል። ወደ ሁለት ሚሊየን የሚገመቱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ፣ 63ሺ ስደተኞች እና 5.2 ሚሊየን ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍን ይሻሉ ። ዮናይትድ ስቴትስ አሰቃቂ ግድያዎችን፣ በቡድን የተፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር (ወንጀሎችን) ፣ በግዳጅ መፈናቀልን እና ሆን ተብለው የሚደረጉ የሰላማዊ ሰዎችን ንብረቶች የማውደም ድርጊቶችን በእጅጉ ታወግዛለች።በትግራይ ክልል ውስጥ የተፈጸሙ ሁሉን ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፣ በደሎች እና ወንጀሎች እናወግዛለን!” ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ የተፈጸሙት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ፣ አማራ ክልላዊ ሰራዊት ፣ የኤርትራ የመከላከያ ሰራዊት እና የትግራይ ህዝቦች ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሐት) አባላት መሆኑን ያወሱት ጎዴክ ፣ የአማራ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ ኃይል አባላት የትግራይ ተወላጆችን ከቤታቸው ማፈናቀላቸው በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ አንተኒ ብሊንከን ዘንድ “የዘር ማጥራት” ድርጊት ተብሎ መጠራቱን አስታውሰዋል። ጎዴክ የኤርትራ ጦርም ያልተቋረጠ ጥቃት እና እንደ ጀምላ ቅጣት የሚቆጠር በደል በትግራይ ህዝቦች ላይ እንፈጸመ ተናግረዋል።

እኒህ ወንጀሎች ሊቀሙ እንደሚገባ በድጋሚ ያሳሰቡት ጎዴክ ፣ ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያው ጫና ጥሪ ጎን ለጎን ሀገራቸው እየወሰደቻቸው ያሉትንና ልትወሰዳቸው የምትችላቸውን ርምጃ ዘርዝረዋል።

“ ለኢትዮጵያ የምንሰጠውን የውጭ ድጋፍ አቅበናል።ይሁንና ሰብዓዊ ድጋፎችን ፣ ጤናን፣ የምግብ ዋስትናን ፥ዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን በሚመለከቱ ወሳኝ መርሐ ግብሮች ላይ የምንሰጠውን ድጋፍ እንቀጥላለን። ለልማት ባንኮች የቀረቡ የብድር ጥያቄዎች፣ መሰረታዊ የሰብዓዊ ፍላጎቶችን የሚመለከቱ እስካልሆኑ ድረስ ተይዘው እንዲቆዩ እያደረግን ነው።አጋሮቻችን ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበናል ” ፣ያሉት ሮበርት ኤፍ ጎዴክ በባለስልጣናት ላይ ስላነጣጠረው የመንግስታቸው እርምጃ ሲያስረዱ ፣ “የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ለገጠመው ችግር የሚሆኑ መፍትሄዎችን የሚያደናቅፉ፣ሰብዓዊ ድጋፎችን የሚያግዱ ወይንም ወንጀሎችን በሚፈጽሙ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ባለስልጣናት፣በአማራ ክልላዊ እና መደበኛ ያልሆነ ጦር እንዲሁም በትግራይ ህዝቦች ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሐት) አባላት ላይ የጉዞ እቀባ አድርጓል። ግጭቱን የሚያባብሱት ከአድራጎታቸው ካልተመለሱ ፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተጨማሪ እርምጃዎችን ይጠብቁ።በትግራይ ጥቃት እና ወንጀል ባለበት ሁኔታ ፣ ነገሮች በተለመደው ሁኔታ አይቀጥሉም ። ” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቀውስ እና የዮናይትድ ስቴትስ የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ምላሽ
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:33 0:00


ዮናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ለሚኖራት ትብብር ብሎም ለሀገሪቱ አንድነት እና ለአፍሪቃ ቀንድ መረጋጋት ቁርጠኛ መሆኗን ያወሱት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ተጠባባቂ ረዳት ጸሃፊ የሆኑት ሮበርት ኤፍ ጎዴክ በትግራይ ክልል ያለውን ውጥረት በተመለከተ ከህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ጋር መስራት እንደሚቀጥሉ አክለዋል።

በስብሰባው ላይ ስለ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ሁኔታ ማብራሪያ የሰጡት ሌላኛዋ ባለ ስልጣን የዮናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ቢሮ ረዳት አስተዳዳሪ የሆኑት ሳራ ቻርለስ ናቸው።

በክልሉ የደረሱ ሁለንተናዊ ችግሮችን በተመሳሳይ የዘረዘሩት አስተዳዳሪዎ ትኩረት ሰጥተው ካጋሯቸው ጉዳዮች አንዱ የጾታዊ ጥቃት መንሰራፋትን ነው።በህይወት ዘመናቸው ካዮቸው የጭካኔ ድርጊቶች አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

“ ሪፖርቶቻችን ስለተንሰራፋው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እና ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ብቻ አይደለም የሚያወሩት። በተቀናጀ ሁኔታ ማህበረሰብን ለማናጋት እና ቤተሰብንም ለማውደም ስለተደረጉ ጥረቶችም ጭምር እንጂ።አንዳንድ ጥቃት አድራሾች የቀሳውስት ሚስቶች ላይ ጥቃታቸው አነጣጥሯል።ሴቶችን በቤተሰቦቻቸው ፊት ጥቃት ይፈጽሙባቸዋል። ወይንም ደግሞ በሴቶች አካል ላይ ጉዳት የሚደርስ ከባድ የጭካኔ ጥቃት ፈጽመዋል ” ሲሉም ግጭቱ እየተወ ስላለው ጠባሳ አስረድተዋል።

ከመሰል ጥቃቶች ወዲያ በክልሉ የግብርና እንቅስቃሴዎች በወጉ እንዳይከናወኑ ግጭቱ በመከልከሉ የክልሉን ነዋሪዎች ወደ ረሃብ ቋፍ እየገፋቸው መሆኑን አውስተዋል።

ዮናይትድ ስቴትስ ከማንም በላይ ለክልሉ ነዋሪዎች የሚሆን ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበች መሆኑን ያወሱት አስተባባሪዎ የምግብ ድጋፍ ብቻውን ግን በትግራይ ክልል ያንዣበበውን ረሃብ ሊያስቀር እንደማይችል ተናግረዋል

“ የምግብ ድጋፍ ብቻውን በትግራይ ክልል ረሃብ እንዳይፈጠር አያከላከልም።ረሀብን ለመከላከል የተቀናጀ የህብረተሰብ ጤና ፣ ስነ ምግብ እና የንጽህና አጠባበቅ አገልግሎቶች ያስፈልጋሉ።በቂ ምግብ፣ንጹህ ውሃ እና መሰረታዊ የጤና እና ምገባ አገልግሎቶች በሌሉበት ፣ በምግብ እጥረት የተጎዱ አካሎች ውጤታማ በሆነ መልኩ ምግቡን ሊጠቀሙበት በሽታንም ሊከላከሉ አይችሉም ”፣ ብለዋል።

የዮናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ በክልሉ ውስጥ መጠነ -ሰፊ ስራዎችን በተለያዩ ዘርፎች ላይ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት የሰብዓዊ ድጋፍ ቢሮ ምክትል አስተዳዳሪዎ ሳራ ቻርለስ ሀገሪቱ ለሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞች የምትሰጠው አጭር የቪዛ ጊዜ ፣በተፈላሚ ወገኖች ዘንድ ሰራተኞቹን በጠላትነት የማየት ክስተቶች እና በቅርቡ የትግራይ ህዝቦች ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሐት) በሽብርተኝነት መፈረጁ በሰብዓዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ የደቀኑትን ፈተና አውስተዋል።

ረዳት አስተዳዳሪዎ በትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄ ቢጨምርም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የቀረበው ገንዘብ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው ለጋሾች ረሃብን ለመመከት ድጋፋቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ መስሪያ ቤታቸው ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዮናይትድ ስቴትስ በ2021 የበጀት ዓመት 650 ሚሊየን ዶላር ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጓን አስታውሰው ፣ በትግራይ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት ግን የ2021 የበጀት ዓመት ሰብዓዊ ድጋፍ በ40 በመቶ ሊጨምር እንደሚችል ገምተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በስብሰባው ላይ በቀረቡ ጉዳዮች ላይ የለውን ምላሽ በቀጣይ መሰናዶወች ለማከታት እንሞክራለን። ቀይሄ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞነኛ የዮናይትድ ስቴትስ እርምጃዎችን ጣልቃ ገብነት ብሎ ከመጥራት ባሻገር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ዳግም ለማጤን ሊያስገድዱት እንደሚችሉ ማስጠንቀቁ ይታወሳል ።

በኤርትራ መንግስት በኩል ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ኦፌሳሊያዊ ምላሽ ባይሰጥም የሀገሪቱ የመረጃ ሚኒስትር የማነ ገ/ መስቀል በቲዊተር ገጻቸው ላይ ይሄንን ብለዋል፣ “ከ ዮናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እስከ ህግ መወሰኛው የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ እና ሌሎች የናይትድ ስቴትስ መንግስት ቅርንጫፎች ድረስ ያለው የአፍሪካ ቀንድን የሚመለከት ወቅታዊ የሀሳብ ልውውጥ በአንድ ጠቅላይ ሀረግ የሚቀመጥ ነው። እሱም ህወሐትን ከቀሰቀሰው የክህደት ጥቃቱ ተወቃሽነት ማዳን እንዲሁም ቅሬቶቱን በአንድም ሆነ በሌላ እንዲንሰራሩ ማድረግ ነው ።” ሲሉ ሰሞነኛውን ሂደት ተቃውመዋል።ወደ አንድ ጎን ያጋደለ አቀራረብ ከዓለም አቀፍ ህጎች ጋር የሚጣረስ መሆኑን ያነሱት የመረጃ ሚኒስትሩ ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋትን የሚጎዳ መሆኑንም አክለዋል።

XS
SM
MD
LG