የአፍሪካ ሃገሮች መላዋን አህጉሪቱን በብርቱ ሊጎዳ ከሚችል ሁለተኛ ዙር የኮቪድ-19 ማዕበል ለመከላከል በሚያደርጉት ዘመቻ በንቃት እንዲከታተሉ ሲል የዓለም የጤና ድርጅት አሳሰበ።
እስከ አሁን በአህጉሪቱ ቁጥሩ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚደርስ ሰው ለኮቪድ-19 መጋለጡን እና ከ120 ሺ በላይ ሌሎች በዚሁ ወረሽኝ ሳቢያ ማለፋቸውን አገሮቹ ይፋ ያደረጓቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ማትሺዲሶ ሞኤቲ እንዳስረዱት ለብዙዎች ህይወት መጥፋት ምክኒያት የሆነው ቫይረስ አሁንም በአህጉሪቱ በአጠቃላይ ደረጃ ሲታይ የጥድፊያ መዛመቱ አዝማሚያ ዝግ አንዳለ መቀጠሉን የቅርብ ጊዜያቱ አኃዞች ይጠቁማሉ።
መልካም የሚመስለውን ዜና በአበረታችነቱ ቢቀበሉም 13 ሃገሮች ውስጥ ግን የወረርሽኙ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን በመጥቀስ አስጠንቅቀዋል።
“በአህጉሪቱ የሚታየው የኮቪድ 19 ተጋላጮች ቁጥር በአንፃራዊ ሁኔታ የተረጋጋ መስሎ በመታየቱ ብቻ ኋላ ላይዘልቅ የሚችል ከንቱ የደህንነት ስሜት ልናሳድር አይገባም። በሕንድ የታየውን የመሰለ ሁለተኛ ዙር የኮቪድ 19 ማዕበል፤ ያስከተለው ውድመት እና የሟቶች ቁጥር፤ እንዲሁም በሌሎች የዓለም አካባቢዎች የሚታየው የስርጭቱ መጨመር ወረርሽኙ በአፍሪቃም ዳግም ሊያንሰራራ የመቻሉ ብርቱ አደጋ አመላካቾች ናቸው፡፡ የወረርሽኙን የጥድፊያ መዛመት የሚያቀጣትሉት አደገኛ ሁኔታዎች እዚህ አፍሪካ ውስጥም አሉና!” ነበር ያሉት - ማትሺዲሶ ሞኤቲ በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር።
ሃገሮች ቀደም ሲል ይከተሏቸው የነበሩ የመከላከያ እርምጃዎችን እያላሉ መሆናቸውን የተናገሩት ሞየቲ ወረርሽኙን በብዛት በማሰራጨት የሚታወቁት ሰዎች በብዛት የሚሰባሰቡባቸው እንቅስቃሴዎች እና የሕዝብ ንቅናቄዎች በጣም እየጨመሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ሞኤቲ አክለውም ከፊል ያህሉ የቫይረሱን በከፍተኛ ደረጃ መዛመት የሚያስከትሉ ማዕበሎች የሚቀሰቀሱባቸው አዝማሚያዎች እንደሚገጥሟቸው የተነበየበትን ጨምሮ የዓለም ጤና ድርጅት በ46 የአፍሪካ አገሮች ያደረገውን ግምገማም አስታውሰዋል። የአፍሪካ አገሮች “በሕንድ ውስጥ እየሆነ ካለው አሳዛኝ ሁኔታ ትምህርት መቅሰም እና ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ነው” ያሉት።
ቁጥራቸው የበዛ ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች እና ራሳቸውን የቀየሩ የቫይረሱ ዝርያዎች በስፋት መሰራጨት በመላዋ ሕንድ ለተዘገበው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኮቪድ 19 ተጋላጭነት ዕጣ እና ህልፈት ምክኒያት መሆኑ አብራርተዋል፡፡ በሌላ በኩል COVAX በተሰኘው ዓለም አቀፍ ፕሮግራም አማካኝነት አብዛኛውን የኮቪድ-19 ክትባቶች ከህንድ ያገኘችው አፍሪካ ህንድ ዛሬ ባለችበት ሁኔታ ሳቢያ ክትባቶችን ወደ ውጭ መላክ በማቋረጧ ያ አቅርቦት ሊደርቅ ችሏል፡፡
COVAX አፍሪካን ጨምሮ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ያለም አገሮች ለአያሌ ሚሊዮኖች የጸረ-ኮቪድ 19 ክትባት ለማዳረስ የታቀደ የክትባት ማከፋፈያ ፕሮግራም ነው፡፡
“ህንድ ህዝቧን በመከተብ የገጠማትን ፈተና ለመወጣት ማቀዷ ማንም የሚረዳው ነው” ያሉት ሞየቲ የእነኚህ ነብስ አድን ክትባቶች መዳረስ መዘግየት ግን በጣም ያሳሰባቸው መሆኑን ገልጠዋል፡፡ “በመሆኑም የኮሮናቫይረስን በከፍተኛ ፍጥነት መዛመት ለመግታት ዕድል እንዲኖራት አፍሪካ አማራጭ አቅርቦቶችን መፈለግ ይኖርባታል” ሲሉ ሞየቲ አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡