በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኮቪድ-19 እና በፖለቲካ አለመረጋጋት የተፈተኑት የኢትዮጵያ ሚዲያ


በኮቪድ-19 እና በፖለቲካ አለመረጋጋት የተፈተኑት የኢትዮጵያ ሚዲያ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:49 0:00

በብዙ ፈተኛዎች ውስጥ የኖረው የኢትዮጵያ ሚዲያ አሁን ደግሞ ዓለምን ባጠቃው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። በተለይ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ በማስታወቂያ እጥረት ምክንያት ገቢ መቀነስ፣ መረጃ የማግኘት ችግር፣ ባልታወቁ አካላት በጋዜጠኞች ላይ የሚደርስ ማስፈራራትና ጥቃት እንዲሁም የሚዲያዎች መዘጋት ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ትልቅ ፈተናዎች ነበሩ።

ፋሲካ ታደሰ ላለፉት ስምንት አመታት በተለያዩ የህትመት ሚዲያዎች ላይ ከጋዜጠኝነት አንስቶ እስከ አዘጋጅነት ድረስ በሀላፊነት ሰርታለች። ሆኖም ያለፈው አንድ አመት ለኢትዮጵያ ሚዲያ እጅግ ፈታኝና ብዙዎችን ከገበያ ያስወጣ እንደነበር ትገልፃለች።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ ትልቅ ተፅእኖ አድርሷል። የኢትዮጵያ ሚዲያም በዚህ ተፅእኖ ስር ከወደቁ የሙያ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ሲሆን የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ የውጪ ንግድ ገቢ መቀነስና የሀገር ውስጥ ምርት አለማደግ ያስከተለው የኢኮኖሚ መዳከም ለማስታወቂያ የሚወጣውን ወጪ በመቀነሱ፣ አስቀድሞም በዲጂታል ሚዲያ መስፋፋት ምክንያት የተዳከመውን ተቋም ከገበያ ውጪ እያደረገው መሆኑን ፋሲካ ታሰምርበታለች።

ከኮሮና ቫይረስ በተጨማሪ ያለፈውን አመት ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ፈታኝ ያደረገው የፖለቲካ አለመረጋጋትና ያንን ተከትሎ የመጣው የደህንነት ችግር ነው። ከዚህ ቀደም መንግስት በሚያወጣቸው አፋኝ ህጎች ምክንያት ለእስር፣ እንግልትና ስደት ይዳረግ የነበረው ሚዲያ አሁን ካልታወቁ ግለሰቦችና ቡድኖች ጥቃትና ዛቻ እንደሚደርስበት በአሻም ቴሌቭዥን ረዳት አዘጋጅ የሆነቸው ካሳዬ ዳምጤ ታስረዳለች።

በኢትዮጵያ ውስጥ በእጅጉ የተንሰራፋው ብሄርን መሰረት ያደረገ ፅንፈኝነት በግልም ሆነ በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ለሚሰሩ ጋዜጠኞች ትልቁ ፈተና እንደሆነ ላለፉት አምስት አመታት በሸገር ሬዲዮ እየሰራች የምትገኘው ምህረት ስዩምም ትስማማበታለች። ኢትዮጵያ ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታ ጋዜጠኛው መሀል ላይ ሆኖ ስራውን እንዳይሰራ እያደረገው ነውም ትላለች።

ፋሲካም እነዚህ ማንነታቸው በውል ካልታወቁ አካላት የሚደርሱ ማስፈፋራቶችና ጥቃቶች፣ ጋዜጠኞች እንደልብ ወደተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው እንዳይዘግቡና ለደህነታቸው እንዲፈሩና እንዳደረጋቸው ትናገራለች።

ሌላው ለረጅም አመታት ሊፈታ ያልቻለውና አሁንም ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ትልቅ ችግር ሆኖ የቀጥለው መረጃ የማግኘት ችግር ነው። ይህ በተለይ ለግል የሚዲያ ተቋማት ፈታኝ እንደሆነና አንዳንዴም ሀገር ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞች መረጃን ከውጪ ሚዲያ ወይም ከማህበራዊ ትስስር ገፆ ላይ እንዲወስዱ እያስገደዳቸው እንደሆነ ካሳዬ ትገልፃለች።

ከላይ የተነሱት ችግሮች እንዳሉ ሆነው ሴት ጋዜጠኞች በሀላፊዎቻቸው ብቁ ሆነው አለመታየት ጀምሮ እስከ የፆታ ትንኮሳዎች የሚደርሱ ተጨማሪ ተግዳሮቶችንም ያስተናግዳሉ። በዚህም በስራቸው ብቁ ሆነው እንዳይታዩ፣ ለሀላፊነት እንዳይታጩ ወይም ሀላፊነት ላይ ቢቀመጡም ከስራቸው ያሉ ሙያተኞች ያለመታዘዝ ችግር እንደሚገጥማቸው ፋሲካ ትናገራለች፣ ፆታዊ ትንኮሳም ጨምሮ።

ምህረትም በዚህ ትስማማለች። ለመረጃ ከሚያገኟቸው ግለሰቦች ጀምሮ እስከማህበራዊ ትስስር ሚዲያዎች ድረስ ሴት ጋዜጤኞች የተለያዩ ፆታዊ ጥቃቶች ይደርስብናል ትላለች።

የሚዲያ ፅንፈኝነት፣ የጋዜጠኞች የሙያ ብቃት እና በነፃነት ዙሪያ የታዩት መሻሻሎች ወደኃላ መቀልበስ ስጋት አሁንም የሚዲያው ፈተናዎች ሆነው ቀጥለዋል። በቅርቡ ፀድቆ የወጣው የመገናኛ ብዙሃን ህግ የተወሰኑ መሻሻሎች ቢታይበትም በተለይ የአቅም መዳከምና ፅንፈኝነት የሚዲያ ተቋማት ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ እንዳያቀርቡና የአንድ አይነት አመለካከት ብቻ መጠቀሚያ እንዲሆኑ እያደረጋቸው እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይመሰክራሉ።

XS
SM
MD
LG