በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ከጥቃት ሊጠበቁ ይገባል - አምባሳደር ግሪንፊልድ


ለህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ከጥቃት ሊጠበቁ ይገባል - አምባሳደር ግሪንፊልድ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:28 0:00

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት ለህዝብ ደህንነትና ህልውና አስፈላጊ የሆኑ ተቋማት ጥበቃ ሊደረገግላቸው በሚችልበት ጉዳይ ላይ ስብሰባ አካሂዷል። በስብሰባው ላይ ንግግር ያደረጉት፣ በመንግስታቱ ድርጅት የዩንናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ፣ ታጣቂ ሀይሎች ሆን ብለው ለህዝብ መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ በመግለፅ ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ታጣቂ ሀይሎች መሰረታዊ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ የሚያደርስቱትን ጥቃት ለመከላከል ማክሰኞ እለት የፀጥታው ምክር ቤት ባደረገው ክርክር ላይ ንግግር ያሰሙት ፣በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ፣ በዓለም ዙሪያ ሰላምና ደህንነት ለማስፈን የሰዎች ደህንነትና ክብር መጠበቁን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የታጠቁ ሀይሎች ሆን ብለው በእርሻዎች፣ የውሀ ማስተላለፊያ ቱቦዎችና የጤና ተቋማት ላይ ቦምብ በመጣል እንደሚያጠቁና ህዝብ መሰረታዊ መገልገያውን እንዲያጣ እንደሚያደርጉ የገለፁት አምባሳደር ግሪንፊልድ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ግጭት እንደማሳያ አቅርበዋል።

"በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያልው ውጊያ የህዝብ መገናኛ አውታሮች እንዲቋረጡ፣ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ሽቦዎች እንዲወድቁ፣ ሆስፒታሎች እንዲዘረፉና ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል። የትግራይ ህዝቦች መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ለደህንነታችው አስጊ የሆኑ በተለይ ፆታዊ ጥቃት የሚፈፀምባቸው ረጅም ጉዞዎች እንዲጓዙ ተገደዋል" ያሉት አምባሳደር ግሪንፊልድ በትግራይ ያለው ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆምም ጠይቀዋል።

በጉዳዩ ላይ ጥያቄ የቀረበላቸው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ወኪል አምባሳደር ታየ አጽቀስላሴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተቻላት አቅም የህዝቦቿ ሰላማዊ ኑሮ እንዳይዛባ እየሰራች መሆኗን ጠቅሰው ፣ “እውነተኛ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ግን ሰላምምን ያወኩ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብለዋል።

አምባሳደር ግሪንፊልድ በንግግራቸው በሶሪያ እየተካሄደ ባለው ግጭት የአሳድ አስተዳደር ከራሽያ በሚያገኘው እርዳታ በሀገሪቱ የሚገኙ መሰረታዊ የልማት ተቋማት ላይ የሚያደርሰውን ውድመት በመግለፅ በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልትም አስረድተዋል። በተለይ በግጭት ጊዜ ትምህርት ቤቶችና የህዝብ ተቋማት ህፃናት ሊጠለሉበት የሚችሏቸው አስፈላጊ ቦታዎች ናቸው ያሉት አምባሳደር ግሪንፊልድ በሶሪያ የገበያ ቦታዎች፣ መኖሪያ ቤቶችና የእምነት ስፍራዎች ሳይቀሩ በመጠቃታቸው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሀገሩ ነዋሪዎች መሰደዳቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በየመን መንገዶች፣ ድልድዮች፣ የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች በመፈራረሳቸው የመን በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ ከፍተኛው ሰብዓዊ ቀውስ ያለበት አገር መሆኗንም ግሪንፊልድ በንግግራቸው አስረድተዋል።

"ይህ በጣም አሰቃቂና ትክክል ያልሆነ ድርጊት ነው" ያሉት ግሪንፊልድ የሲቪሎችን ደህንነት ለመጠበቅ እንደዚህ አይነት ድርጊት በመፈፀም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህጎችን የሚጥሱ ቡድኖችን ተጠያቂ ማድረግ አለብን ብለዋል።

XS
SM
MD
LG