በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኘው ኮቪድ-19


በኢትዮጵያ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኘው ኮቪድ-19
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:00 0:00

በኢትዮጵያበኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን በበሽታው ምክንያት ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡና ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ቀጥሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ውስጥ የፅኑ ህሙማን አልጋ፣ ኦክስጅንና ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች እጥረት የተከሰተ ሲሆን የቫይረሱ ተጠቂዎች ህክምና ለማግኘት መቸገራቸውን የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የታማሚ ቤተሰቦች ተናግረዋል።

መክሊት ምንተስኖት በሞጆ የሚኖሩ እናቷን ለቀናት እረፍት ለነሳቸው ህመም የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ ወደ አዲስ አበባ ብታመጣቸውም ምክንያቱ ግን ሊታወቅ አልቻለም። ይታከሙበት የነበረው ዋሽንግተን ሆስፒታልም የአልጋና የኦክስጅን እጥረት ስላጋጠመው ለተሻለ እርዳታ ወደ ካዲስኮ ይመራቸዋል።

መክሊትና ቤተሰቦቿ በካዲስኮም የገጠማቸው ተመሳሳይ ነው። ሆስፒታሉ ኦክስጅንና የፅኑ ህሙማን አልጋ በሚፈልጉ በሽተኞች ተጨናንቋል። በድንገተኛ ለተለያዩ ህክምና ለሚመጡ በሽተኞችም ቦታ የላቸውም። የመክሊት እናት በተደረገላቸው ምርመራ የኦክስጅን መጠናቸው ከ60 በታችም መሆኑ ቢነገራቸውም፣ ተኝተው የሚታከሙበት አልጋም ሆነ ለመተንፈስ የሚረዳቸው ኦክስጅን አልነበረም። መክሊት "በዚህ መሀል እናቴ በጣም እየደከመች ሄደች" ትላለች።

ኮሪያ ሆስፒታልም የተለየ ሁኔታ አልገጠማቸውም። እዛም አልጋ የለም፣ ኦክስጅንም አልነበረም።

በእናታቸው ከፍተኛ መዳከም የተደናገጠው የመክሊት ቤተሰብ በተለያዩ ሆስፒታሎች ለእናታቸው እርዳታ ለማግኘት ብዙ ከለፉ በኃላ በመጨረሻ ሚኒሊክ ሆስፒታል ኦክስጅን ማግኘት እንደቻሉ መክሊት ትናገራለች።

መክሊትና ቤተሰቧ ባለፈው ሳምንት ያሳለፈው ውጣ ውረድ ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ስርጭቱን በጨመረው ኪቪድ ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን እያሳለፉት ያለው ችግር ነው። ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢትስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የሚጠቃው ሰው ቁጥር በ 20 በመቶ ጨምሯል - ይህ ማለት ምርመራ ከተደረገላቸው ከሶስት ሰዎች አንዱ በኮቪድ-19 መያዙን ያሳያል ሲልም አስጠንቋል።

በዚህ ሳቢያ ሆስፒታሎች የህክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ፅኑ ህሙማን መርጃ የሚያገለግሉ የመታከሚያ አልጋዎች፣ የሰው ሰራሽ መተንፈሻ መርጃ (ቬንትሌተር) እና ኦክሲጂን እጥረት አጋጥሟቸዋል። ከነዚህ መሀል ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጊዜ አንስቶ ለፅኑ ህሙማን አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ቅዱስ ጳውሎስ ሆፒታል አንዱ ነው። በየእለቱ በሆስፒታሉ በፅኑ ህሙማን መርጃ ውስጥ ከሚታከሙ ሰዎች እጥፍ የሚሆኑ አገልግሎቱን ለማግኘት እየተጠባበቁ መሆናቸውን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የድንግተኛና ፅኑ ህሙማን ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰና ሀኪም የሆኑት ዶክተር መንበዑ ሱልጣን ነግረውናል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተጨማሪ ለፅኑ ህሙማን የሚሆኑ አልጋዎችን ለመጨመርና አገልግሎቱን ለማስፋት እየታሰበ ቢሆንም፣ ከዛ ጎን ለጎን የሚያፈልጉ የህክምና ግብዓቶችን ማግኘት ግን አስቸጋሪ እንደሚሆን ዶክተር መንበዑ ይገልፃሉ።

የኮቪድ 19 ታማሚዎች በግል ሆስፒታሎች ህክምናውን ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር እንደሚያስወጣ በርካቶች ነግረውናል። አዲስ አበባ ውስጥ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ነዋሪ የሆነው አዲስ አጋ ወንድሙ በኮቪድ-19 መያዙን ካረጋገጠ በኃላ በግል ለማሳከም ሞክሮ ነበር።

አዲስ ወንድሙ በጳውሎስ ሆስፒታል ክትትል ቢደረግለትም ነፍሱ ግን ሊተርፍ እንዳልቻለ ይናገራል - ሆኖም በኛ ቤት የደረሰው በሌላው ቤት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲል ይመክራል።

ዶክተር መንቡዕ እንደሚሉት ይህ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ የመጣው የኮቪድ 19 ስርጭትና በህክምና ተቋማት ላይ እያሳደረ ያለው ጫና ለሌሎች በሽታዎች የሚሰጡ ህክምናዎች ላይም ተፅእኖ እያሳደረ ነው። ጥናቶች ገና ባይጠኑም የህክምና ባለሙያዎች ላይም የአካልና የመንፈስ መዳከም እያመጣ እንደሆነም ያሰምሩበታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እለታዊ መረጃ እንደሚያሳየውም በአሁኑ ሰዓት ከ841 በላይ ግለቦች በኮቪድ 19 ተይዘው ፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ። በመሆኑም ህብረተሰቡ ማስክ በማድረግ፣ እጆችን በየጊዜው በመታጠብና እርቀትን በመጠበቅ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንዲጠብቁ ሁሉም ይመክራሉ።

XS
SM
MD
LG