በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ረሃብ አድማ ላይ ያሉት ሩሲያዊው አሌክስ ናቫልኒ ሆስፒታል ገቡ


ፎቶ ፋይል፦ ሩስያው ተቃዋሚ መሪ አሌክሲ ናቫልኒ
ፎቶ ፋይል፦ ሩስያው ተቃዋሚ መሪ አሌክሲ ናቫልኒ

በእስር ቤት የረሃብ አድማ ላይ ያሉት የሩስያው ተቃዋሚ መሪ አሌክሲ ናቫልኒ ወህኒ ቤቱ ሆስፒታል ገብተዋል። ባልደረቦቻቸው ግን ደህና ወሬ እንሰማለን የሚል ተስፋ የለንም በማለት አስጠንቅቀዋል።

ዛሬ የሩስያ የወህኒ ቤቶች ባለሥልጣናት በሰጡት ነው ናቫልኒን ሆስፒታል አስገብተናቸዋል ያሉት። የፌዴራል ወህኒ ቤቶች መምሪያው ባወጣው መግለጫ

"ባሁኑ ሰዓት ናቫልኒ አጥጋቢ የጤና ሁኔታ ላይ ናቸው፣ ሃኪሞች በየቀኑ እየተከታተሉዋቸው ናቸው፣ በፈቃዳቸው የቫይታሚን ህክምና እየተሰጣቸው ነው” ብለዋል።

ተቃዋሚ መሪው ከሞስኮ በስተምስራቅ ወደሚገኝ በከባድ ጥበቃ ሥር የሚገኝ ሆስፒታል መግባታቸውን በሚመለከት ከደጋፊዎቻቸው በኩል ለጊዜው የተሰማ አስተያየት የለም ዛሬ ቀደም ብሎ ግን አንድ የናቫልኒ ባልደረባ

“ስለጤናቸው ደህና ወሬ እንሰማለን ብዬ አልጠብቅም" ብለው ነበር።

ረሃብ አድማ ላይ የቆዩት አሌክሲ ናቫልኒ ለልብ ድካም ወይም ለኩላሊት ከጥቅም የመሆን የከበደ አደጋ ላይ እንዳሉ የሚጠቁም የደም ምርመራ ውጤት ቤተሰቦቻቸው እና የግል ሃኪሞቻቸው ይፋ አድርገዋል። ይህንኑ ተከትሎ ደጋፊዎቻቸው ሀገር አቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርተዋል።

የተቃውሞ ሰልፉ የተጠራው ታዲያ ለተነገ ወዲያ ረቡዕ ሲሆን ቀኑ የሩስያ ፕሬዚደንት ቪላዲሚር ፑቲን ከክሬምሊን ቤተ መንግሥት አጠገብ ዓመታዊ የሀገር ሁኔታ መግለጫ ንግግራቸውን የሚያደርጉበት ዕለት ነው። በመሆኑም በመዲናዋ ሞስኮ በናቫልኒ ደጋፊዎች እና በፖሊሶች መካከል ከባድ ፍጥጫ እንደማይቀር ተዘግቧል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የናቫልኒ ሃኪሞች ይፋ ያደረጉት የደም ምርመራ ውጤታቸው የሚያሳየው የፖታሲየም መጠን እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ እንዳለ ያሳያል። ይህም በማናቸውም ደቂቃ የልብ አመታት ችግር ወይም የኩላሊት እክል ሊከሰት ይችላል፤ በፍጥነት ካልታከሙ በቀናት ጊዜ ውስጥ ህይወታቸው ሊያልፍ ይችላል ሲሉ ሃኪሞቹ በፊርማቸው ባወጡት ደብዳቤ አሳስበዋል።

የሁለት ዐመት ተኩል እስራት ተፈርዶባቸው ከሞስኮ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ወህኒ ቤት የሚገኙት የአርባ አራት ዓመቱ አሌክሲ ናቫልኒ ህክምና እንዲያገኙ በመጠየቅ የረሃብ አድማውን ከጀመሩ ሦስተኛ ሳምንታቸውን ይዘዋል። ዓርብ ዕለት ባለሥልጣናቱ 'በግድ ትበላለህ' እያሉ እየዛቱብኝ ነው ብለው ነበር። ቀደም ብሎም "ከረሜላ ኪሴ ውስጥ እየከተቱ እና ዶሮ እየጠበሱ ሊያስጎመዡኝ እየሞከሩ ነው" ሲሉ ተናግረው ነበር።

ተቃዋሚ መሪው ከባድ የወገብ ህመም እና የእግር መደንዘዝ እንዳለባቸው ለሳምንታት ሲናገሩ ቆይተዋል። ጠበቆቻቸው እንዳሉት ከባድ ሳልና ማዞርም አለባቸው፥ ናቫልኒ የህመማቸው ምክንያት ባለፈው ነሃሴ ከደረሰባቸው የመርዝ ጥቃት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይናገራሉ፥ እሳቸው እና ምዕራባውያን መንግሥታት የመርዝ ጥቃቱ ተጠያቂ የሩስያ መንግሥት እንደሆነ ተናግረዋል። ክሬምሊን ቤተ መንግሥት በበኩሉ እጃችን የለበትም። ስለመመረዛቸው ማረጋገጫም የለም በማለት ምርመራ አናካሂድም ብሏል።

የሩስያ መንግሥት አሌክሲ ናቫልኒ ያሉበት የእስር ሁኔታ መልካም እንደሆነ እንዲያሳዩ እና ናቫልኒ ታምሜአለሁ የሚሉት ከሌሎቹ የተለየ አያያዝ እንዲሰጣቸው ነው የሚሉ ሪፖርቶች የሚያወጡ የመንግሥት ዜና ማስራጫዎችን ማሰማራቱ ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG