ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝብ የድል ተምሳሌት ተደርጎ የሚቆጠረው አድዋ፣ ኢትዮጵያውያን ከሀገሪቱ አራት ማዕዘናት ተጠራርተው በሙሉ ፈቃደኝነት የውጪ ወረራን የመከቱበት የድል በዓል ነው። የፊታችን ማክሰኞ የዚህ ድል በዓል 125ኛ አመት ሲከበርም ይህን የበጎ ፈቃደኝነት መንፈስ አጉልቶ ለማሳየት እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
ልዩነቶች ጎልተው በሚታዩበት በዚህ ትውልድ ድምበር የለሽ ሆኖ የማገልገልን ልምድ ከአድዋ እንማር በሚል መነሻ እንቅስቃሴውን ከፊት ሆነው ከሚመሩት መሃል እራሳቸውን በጎ ፈቃደኛና ባለእዳ ብለው የሚጠሩት ታምሩ ደገፋ ናቸው።
የፊታችን ሰኞ የአድዋ በዓልን ለማሰብ በጎ ፈቃደኝነትን ማዕከል አድርጎ የተዘጋጀው ይህ ዝግጅት የአካባቢን ንፅህና መጠበቅን፣ ልዩ እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ድጋፍ መስጠትንና ተማሪዎችን ስለበጎ ፈቃደኝነት ማሰልጠን እንደሚያካትት በጎፈቃደኛ ታምሩ ይገልፃሉ።
በጎፈቃደኛ ታምሩ ህዝብን በነፃ የማገልገል በጎ ስራ የጀመሩት ከ18 አመት በፊት ለበርካታ አመታት በኖሩበት አሜሪካን አገር እያሉ ነበር። በዋሽንግተን ዲሲ፣ ቨርጂንያ እና ሜሪላንድ አካባቢ መርካቶ በሚለው የንግድ ተቋማቸው ይታወቁ የነበሩት የአሁኑ በጎ ፈቃደኛ ታምሩ ወደ ኢትዮጵያ ከመመለሳቸው በፊት በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማዕከል፣ እንዲሁም ከተለያዩ ሀገር ዜጎች ጋር በመሆን የሰላምና አረንጓዴ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ይሳተፉ እንደነበር ያስታውሳሉ። ሙሉ ሰዓታቸውን ለበጎ ፈቃድ ማዋል የጀመሩት ግን ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኃላ ነው።
በጎ ፈቃደኛ ታምሩ ድርጅት አያቋቁሙ እንጂ የሚሰሯቸውን የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴዎች የሚያከናውኑት እንደእሳቸው ተመሳሳይ አላማ ካላቸው ግለሰቦች፣ ማህበራትና ድርጅቶች ጋር ነው። የሚያከናውኗቸው በጎ ተግባራትም በአብዛኛው በመንግስትም ሆነ በሌሎች አካላት ያልታዩ ክፍተቶችን የሚሞሉና መልካምነትን ለሌላው የሚያስተምሩ እንደሆኑ ይገልፃሉ።
በተለይ ከቅርብ ግዜ ውዲህ በዘር፣ በሀይማኖትና በማንንነት በመከፋፈል ምክንያት የሚደርሱ ግጭቶች በበረከቱባት ኢትዮጵያ በጎፈቃደኝነት፣ ልዩነትን ማጥበቢያና ሰዋዊ ማንነት ማሳደጊያ ነው የሚሉት በጎፈቃደኛ ታምሩ አንድ በመሆን ለሚገኘው ድል ማሳያ ከአድዋ በላይ እንደሌለ ያስረዳሉ።
አድዋን አስመልክቶ ሰኞ በሚካሄደው የበጎ ፈቃደኛነት መርሃ ግብር ከአዲስ አበባ ክፍለተሞች የተውጣጡ በጎ ፈቃደኞች፣ የአዲስ አበባ ስካውት ማህበር፣ ሴንተር ፎር ፋሚሊ ሰርቪስ የበጎ አድራጎት ድርጅትና ሌሎች በበጎ አድራጎት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ይሳተፋሉ።