በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች አካታች የትምህርት ተቋማት ይፈልጋሉ


ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች አካታች የትምህርት ተቋማት ይፈልጋሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:07 0:00

ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች እንደየፍላጎታቸው የሚያስተምሩ አካታች ትምህርት ቤቶች በስፋት ባለመኖራቸው ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ህፃናት ተገቢውን ድጋፍ እንደማያገኙ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በማህበረሰቡ ዘንድ ባለው የግንዝቤ እጥረትና የአቅም ማነስም ህፃናቱንና ቤተሰቦቻቸው ለበርካታ ችግሮች ይጋለጣሉ። ይህን ችግር ለመቅረፍ ሻምፒዮንስ አካዳሚ የተሰኘ አካታች የግል ተቋም አርዓያ የሚሆኑ ተግባራትን እየሰራ ይገኛል።

ወይዘሮ አልማዝ ጥላሁን ከሶስት ልጆቻቸው የመጀመሪያ የሆነው የ16 አመት ልጃቸው ልዩ ፍላጎት እንዳለው ያወቁት አራት አመት ሲሞላው ነበር። ልጃቸው እስከ እዛ እድሜው መናገርና እራሱን መግለፅ ካለመቻሉ በላይ በጣም ብስጩ መሆኑ ያሳሰባቸው ወይዘሮ አልማዝ ተመርምሮ የኦቲዝም ተጠቂ መሆኑ እስከሚነገራቸው ድረስ ስለበሽታው ሰምተው እንደማያውቁ ይናገራሉ።

ስለልጃቸው ልዩ ፍላጎት ዘግይተውም ቢሆን የተረዱት ወይዘሮ አልማዝ አሁንም ድረስ ፈተና የሆነባቸው ግን የልጃቸው ትምህርት ጉዳይ ነው። በሚኖሩበት አስኮ አካባቢ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ልጆች ትምህርት የሚሰጥ ምንም አይነት ትምህርት ቤት የለም። በመንግስት ሰራተኛ ደሞዛቸው በወር 6ሺህ ብር የሚከፈልበት የግል ትምህርት ለማስገባት ያደረጉት ጥረት ደግሞ ከአቅማቸው ጋር መሄድ እንዳልቻለ በሀዘን ይገልፃሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ልክ እንደወይዘሮ አልማዝ ልጅ ልዩ ፍላጎት ያላቸው፣ ልዩ እንክብካቤና ድጋፍ የሚሹ ወደ 23 ሚሊዮን ሰዎች ቢኖሩም ብዙዎቹ ትምህርት ለማግኘት እንደሚቸገሩ የአይምሮ ህክምና ባለሙያና አማካሪ የሆኑት ዶክተር መዓዛ መንክር ይናገራሉ።

ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች የሚታይ አካላዊ ጉዳት ወይም የማይታይ የባህሪ፣ ስሜትና አይምሮ እድገት ችግር ያለባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ህፃናት ታዲያ ትምህርታቸውን ለመከታተል የሰለጠነ ባለሙያ፣ ለነሱ ተብሎ የተዘጋጀ የማስተማሪያ ቁሳቁስ እና የተለየ የመማር ማስተማር ሂደት ይፈልጋሉ። ይህን ለማሟላት በመንግስት ደረጃ የአካታች ትምህርት ፖሊሲ ተቀርፆ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የልዩ ፍላጎት መምህርነት በተለያየ ደረጃ ቢሰጡም ለምን ወደ መሬት ወርዶ ተግባር ላይ እንደማይውል ግን ዶክተር መዓዛ ያስረዳሉ።

የወይዘሮ አልማዝም የዘወትር ጭንቀት ተገቢውን የትምህርት ድጋፍ ማግኘት ያልቻለው ልጃቸው ነገ ምን ይሆናል የሚለው ሀሳብ ነው።

ይህን ችግር በጥቂቱም ቢሆን ለመቅረፍ የክሊኒካል ሳይኮሎጂ ምሩቅ የሆኑት ዶክተር መዓዛ የዛሬ 14 አመት አዲስ አበባ ጀሞ አካባቢ በከፈቱት ሻምፒዮንስ አካዳሚ ትምህርት ቤት ወደ 60 የሚሆኑ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ህፃናት ተቀብለው ያስተምራሉ። ከትምህርት ቤት ውጪም ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ህፃናት፣ ወላጆችና መምህራንን በማሰልጠንና ተከታታይ ድጋፍ በማድረግ ስኬታማ ልጆችን እያፈሩ፣ ለማህበረሰቡም ድጋፍ እያደረጉ ነው።

ከዶክተር መዓዛ በተጨማሪ ሴንተር ፎር ፋሚሊ ሰርፊስ የተሰኘ ድርጅትም ማህበረሰቡን ልዩ ፍላጎት ስላላቸው ልጆች ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ችግር ውስጥ ያሉ ቤተሰቦችን የማገዝና ትምህርት ቤቶች አካታች እንዲሆኑ የማድረግ አዲስ እንቅስቃሴ መጀመሩን የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ሀይሉ ነግረውናል።

ልዩ ፍላጎት ይላቸው ህፃናት ተገቢውን ትምህርት እንዲያገኙ እንደ ተጎጂ ሳይሆን አስተዋፅኦ አድራጊ ዜጋ መታየት መጀመር አለባቸው የሚሉት ባለሙያዎች በወላጆችና ማህበረሰቡ ዙሪያ ያለው ግንዛቤ እንዲያድግና መንግስትም ለሌላው የማህበረሰብ አካላት የሚሰጠውን ትኩረት ሰጥቶ አካታች ትምህርት ቤቶች እንዲበራከቱ እንዲያደርግ መክረዋል።
XS
SM
MD
LG