በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የነፃ ትምህርት ቤት የከፈተው የ22 ዓመት ወጣት


በሰሜን ሸዋ፣ ደብረ ፅጌ ከተማ በነፃ ህፃናትን የሚያስተምረው ቅዱስ ትምህርት
በሰሜን ሸዋ፣ ደብረ ፅጌ ከተማ በነፃ ህፃናትን የሚያስተምረው ቅዱስ ትምህርት

የ22 ዓመቱ ወጣት ቅዱስ አንተነህ በአሜሪካን ሀገር ሜሪላንድ ዩንቨርስቲ የኮምፒውተር ሳይንስ እና የሂሳብ የ3ኛ አመት ተማሪ ሲሆን በኢትዮጵያ ትምህርት ቤት በሌለበት የገጠሪቱ ክፍል ትምርህርት ቤት በመክፈት ህፃናት በነፃ ትምህርት እንዲያገኙ እይረዳ ይገኛል። በሚኖርበት ሜሪላንድ ክፍለ ግዛትም በሚሰጠው የማስጠናት አገልግሎት ለበርካታ ተማሪዎች እገዛ ያደርጋል።

በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የነፃ ትምህርት ቤት የከፈተው የ22 አመት ወጣት
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:53 0:00

በሰሜን ሸዋ፣ ደብረ ፅጌ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የሁለት ልጆች አባት አቶ አሰፋ ቀናው የሚተዳደሩት በቀን ስራ ነው። ከእጅ ወደ አፍ በሆነችው ገቢያቸው ሰባት ዓመት የሞላውን የመጀመሪያ ልጃቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባት ሞክረዋል። ነገር ግን "በወር የሚከፈለውን 400 ብር ለመክፈል እጅ ስላጠረኝ ልጄ ትምህርቱን አቋረጠ" ይላሉ።

በልጃቸው ትምህርት ማቋረጥ ልባቸው ተሰብሮ የነበሩት አቶ አሰፋ ግን ባለፈው ዓመት በአቅራቢያቸው በተከፈተው ቅዱስ ትምህርት ቤት ተስፋቸው እንደገና ተመልሶላቸዋል። ልጃቸው በነፃ ትምህርት ከማግኘቱ በተጨማሪ በቀን አንድ ጊዜ በትምህርት ቤቱ ይመገባል፣ የሚያስፈልገው መፅሀፎችና የትምህርት መሳሪያዎችም ይሟሉለታል።

"ቅዱስ ትምህርት ቤት" ከደብረ ፅጌ ከተማ አለፍ ብሎ ወደ ደብረሊባኖስ በሚወስደው መንገድ ላይ በአካባቢው ላሉና ትምህርት ማግኘት ላልቻሉ ህፃናት የነፃ ትምህርት አገልግሎት እንዲሰጥ የከፈተው የ22 ዓመቱ ወጣት ቅዱስ አንተነህ ነው።

ገና ከህፃንነት እድሜው አንስቶ ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን በተለያዩ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ክፍሎች ድብተርና መፃፊያዎች የመሳሰሉ የትምህርት ቁሳቁሶችን ይሰጥ የነበረው ቅዱስ ዘላቂነት ያለው የህፃናትን ህይወት መቀየር የሚችል ውጤት ለማምጣት ትምህርት ቤቱን እንደከፈተ ይናገራል።

ቅዱስ በትምህርት ዙሪያ ስራዎችን ሲሰራ የደብረፅጌው ትምህርት ቤት የመጀመሪያው አይደለም፣ ሰዎችን መርዳትና በትምህርት ማገዝ ከልጅነቴ ያስደስተኝ ነበር የሚለው ቅዱስ አሁን በሚኖርበት አሜሪካን አገር ሜሪላንድ ክፍለ ግዛት ውስጥ በከፈተው ሜሪላንድ የአስጠኚ አገልግሎት በአሜሪካን አገር በየትኛውም ክፍለግዛት ለሚገኙ፣ ከህፃናት መዋያ እስከ ኮሎጅ ድረስ ያሉ ተማሪዎች፣ የማስጠናት አገልግሎት ይሰጣል።

ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎችን በትርፍ ሰዓት ቀጥሮ በአስጠኚነት የሚያሰራው የሜሪላንድ አስጠኚ አገልግሎት በተለይ በአሁኑ ሰዓት በኮሮና ምክንያት የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደቱን ወደ በይነ መረብ በመቀየራቸው ምክንያት የትምህርት አቀባበል ዙሪያ ለተቸገሩ ተማሪዎችም ጠንካራ ድጋፍ ያደርጋል።

በዚህ የማስጠናት አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑት መሃከል በካሊፎርኒያ ክፍለግዛት ሳኖዜ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሽፈራው ተካ አንዱ ናቸው። አቶ ሽፈራው የ9ኛ ክፍል ተማሪ ልጃቸው በበይነ መረብ አማካኝነት በሚሰጠው የስነ ፅሁፍ ትምህርት እገዛ እንደሚያስፈልገው በመረዳታቸው የሜሪላንድ አስጠኚ አገልግሎትን እንዳናገሩ ይናገራሉ።

በአሜሪካን ሀገር የማስጠናት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በሰዓት እስከ 200 የአሜሪካን ዶላር ያስከፍላሉ። በዚህም ምክንያት ብዙ ወላጆች መክፈል ባለመቻላቸው ለልጆቻቸው የሚያስፈልገውን ድጋፍ ማግኘት ሲያቅታቸው ማስተዋሉን ቅዱስ ይናገራል። ታዲያ እሱ በሚሰጠው አገልግሎት በሰዓት ከ 35 ዶላር ጀምሮ እንደ የትምህርት ደረጃው ዝቅተኛ የአገልግሎት ክፍያ ይጠይቃል።

ቅዱስ በትምህርቱ ባለው ከፍተኛ ውጤት ባመጣለት ነፃ የትምህርት እድል በሜሪላንድ ዩንቨርስቲ የ3ኛ አመት የኮምፒውተር ሳይንስና ሂሳብ ተማሪ ነው። ትምህርቱን ሲያጠናቅቅም የሰው ሰራሽ ልህቀትን ተጠቅሞ ትምህርትን ማስፋፋት የሚቻልበት መንገድ ላይ መስራት እንደሚፈልግ ይናገራል። በትምህርት ዙሪያ የጀመርኳቸውን በጎ ስራዎችም ማሳደግ እፈልጋለሁ የሚለው ቅዱስ በሱ እድሜ ያሉ ወጣቶች በሚችሏቸው ማንኛውም ስራዎች ጠንክረው ቢሰሩ እድሜ ሳያግዳቸው ውጤታማ እንደሚሆኑ ይመክራል።

XS
SM
MD
LG