እሮብ እለት በዩናይትድ ስቴትስ ምክርቤት በተፈጠረው ሁከት የአውሮፓ ወዳጅ ሀገራት መሪዎች ድንጋጤያቸውን እየገለፁ ነው። ከነዚህ መሃከል የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ሁኔታው አሜሪካንን አይወክልም ብለዋል።
"ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ የተፈጠረው ነገር፣ በእውነቱ አሜሪካን የሚገልፅ አይደለም።"
የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ማርኬል በበኩላቸው ዲሞክራሲ በተፈጠረው ነገር እንደማይሸነፍ ተናግረዋል።
"ዲሞክራሲ ከአጥቂዎችና ሁከት ፈጣሪዎች የበለጠ ጠንካራ ነው።"
በትዊተር ገፃቸውን ላይ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቦሪስ ጆንሰንም በተመሳሳይ በአሜሪካ የተፈጠረውን ሁከት 'የሚያሳፍር' ሲል ገልፀውታል። የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ፕሪቲ ፓቴል ደግሞ ለሁኔታው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ተጠያቂ አድርገዋል።
"የእሳቸው ንግግሮች ናቸው ወደ ሁለት እንዲያመሩ ያደረጋቸው ነገር ግን እስካሁን ድረስ የሆነውን ነገር አላወገዙም። ይህ ደግሞ ፍፁም ስህተት ነው። "
ሌላው በአሜሪካ በተፈጠረው አስደንጋጭ ሁከት ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ፣ በምፅሀረ ቃሉ ኔቶ በመባል የሚታወቀው 29 አባል አገራት ያሉት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ የንስ ስቶልትንበርግ ናቸው። ስቶልትንበርግ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ "በዋሽንግተን ዲሲ የታየው በጣም አስደንጋጭ ነው። በአሜሪካ በዲሞክራሲ መንገድ የተዳሄድው ምርጫ ውጤት ሊከበር ይገባል" ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በቃል አቀባዩ አማካኝነት "የፓለቲካ አመራሮች ተከታዮቻቸው ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዳያመሩ የማድረግ ሀልፊነት አለባቸው" በማለት በዚሁ በአሜሪካ በተፈጠረው ሁከት ዙሪያ ላይ አስተያየቱን ሰጥቷል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንጃሚን ኔታንያሁም አጋር ሀገራቸው በሆነችው አሜሪካ የተፈጠረው ከሀገሪቱ መርሆ ጋር የማይሄድ ነው ብለዋል።
"ሁሌም የሚያነቃቃኝ ነገር ቢኖር የአሜሪካ ዲሞክራሲ ነው። ህገ-ወጥነትና ብጥብጥ ከአሜሪካውያን እሴቶችና እስራኤላውያን ከፍተኛ ዋጋ ከሚሰጡት መርሆ ጋር ፍፁም የሚጥረስ ነው። "
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ናሬንድራ ሞዲ ደግሞ በትዊተር ገፃቸው ላይ የዲሞክራሲ ሂደት በህገወጥ ተቃውሞ እንዲቀለበስ ሊፈቀድ አይገባም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ በተፈጠረው ሁከት ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡት ወዳጅ ሀገራት ብቻ አይደሉም። የተቀናቃኝ ሀገራት መሪዎችም ዋሽንግተንን እየወረፉ ናቸው። ከነዚህም መሀከል የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሀሰን ራውኒ በቴሌቭዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር "የተፈጠረው ነገር የምዕራቡ አለም ዲሞክራሲ ምን ያክል በቀላሉ ተሰባሪ መሆኑን ያሳየ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። ቬንዙዌላ ዩናይትድ ሴቴትስ ያጋጠማት በሌሎች ሀገራት ውስጥ የምትጭረው ጠብ ነው ስትል መግለጫ ስታወጣ፣ ቻይና በበኩሏ ነገሩን ለመጠምዘዝ ሞክራለች።
"የዩናይትድ ስቴትስ መገናኛ ብዙሃን ባንድ ድምፅ የተፈጠረውን ሁከት ወንበዴዎች፣ አክራሪዎች፣ እኩይ ባህሪ እና አሳፋሪ የመሳሰሉ ቃላትን በመጠቀም አውግዘውተዋል። ግን በሆንግ ኮንግ ሁከት ያስነሱ ተቃዋሚዎችን ለመግለፅ የተጠቀሟቸው ቃላቶች ምንድናቸው? የሚያምር እይታ ነው ብለው ነበር፣ ሁከት ፈጣሪ ተቃዋሚዎችን እንደ ጀግና አቅርበው አሜሪካ ከጎናቸው ትቆማለች ነበር ያሉት።"
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የሞስኮ አምባሳደር የሆኑት ዲሚትሪ ፖሊአንስኪም በአሜሪካ የተፈጠረውን እ.አ.አ በ2014 በዩክሬይን ከነበረው አብዮት ጋር በማወዳደር ተመሳሳይ ሁኔታዎች በዋሽንግተን ዲሲ እየታዩ ነው ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ ፅፈዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ወዳጆች አብዛኞቹ አሜሪካውያን በዲሞክራሲያቸው ላይ በደረሰው ሁከት የተሰማቸውን ህመም ይጋራሉ። ጠላቶቿ ግን የተፈጠረውን ክስተት የፖለቲካ ውጤት ለማስቆጠር እንደ እድል እየተጠቀሙበት ነው።