በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሳይንስ ውድድር $400 ሺህ ዶላር ያሸነፈችው የ17 አመት ወጣት


በሳይንስ ውድድር $400 ሺህ ዶላር ያሸነፈችው የ17 አመት ወጣት
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:51 0:00

በአለም ዙሪያ ያሉ በአስራዎች እድሜ የሚገኙ እና ለ ሳይንስና ለሂሳብ ትምህርት ፍቅር ያላቸው ልጆች በየአመቱ የሚወዳደሩበት ብሬክ ስሩ ጁኒየር ቻሌንጅ የተሰኘ የጥሎ ማለፍ ውድድር የዘንድሮ አመት አሸናፊ፣ በካናዳ አገር ተወልዳ ያደገቸው ማሪያም ሞገስ ፀጋዬ ስትሆን በአጠቃላይ የ 400 ሺህ ዶላር ሽልማት አግኝታለች። ከአለም ዙሪያ ከተወዳደሩ 5600 ተማሪዎች መሀል አንደኛ ወጥታ ይህስ ስኬት ያገኘችው ማሪያምንና ወላጅ እናቷን መርሃዊት እዮብን አነጋግረናቸዋል።

ካናዳ ውስጥ ተወልዳ ያደገችው የ 17 አመቷ ማሪያም ሞገስ ፀጋዬ ለመጀመሪያ ጊዜ በተወዳደረችበት አለም አቀፍ የሳይንስና ሂሳብ ትምህርት ውድድር ማሸነፏን የሰማችው ጥቂት ተማሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው በተቀመጡበት የትምህርት ቤቷ ክፍል ውስጥ በቪዲዮ አማካኝነት ነው።

ለትምህርት ቤቱ ገቢ የማሰባሰቢያ ስራ ላይ ለመሳተፍ በሚል ሰበብ ተጠርታ በቦታው የተገኘችው ማርያም ውድድሩን እንዳሸነፈች ሲነገራት በድንጋጤና ባለማመን ግራ ስትጋባ የውድድሩ አዘጋጆች በለቀቁት ቪዲዮ ላይ ይታያል።

በአለም ዙሪያ የሚገኙ ከ 13 -18 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች የሳይንስ ወይም የሂሳብ ጽንሰ ሀሳቦችን የሚያስረዳ የ ሶስት ደቂቃ ቪዲዮ በማዘጋጀት በሚወዳደሩበት ውድድር ማሪያም ያሸነፈችው ኩዋንተም ተነሊግ የተሰኘ የፊዚክስ ፅንሰ ሀሳብን በግሏ አጥንታና ተረድታ፣ በቀላልና ለማንኛውም ሰው በሚገባ መልኩ ማስረዳት በመቻሏ ነው።

በ 124 አገራት የሚገኙ 5600 ተማሪዎች በተሳተፉበት የዘንድሮ አመት ውድድር ማሪያም አንደኛ ሆና በማሸነፏ በአጠቃላይ $400 ሺህ ዶላር የተሸለመች ሲሆን 250 ሺህ ዶላሩ የሷን ትምህርት ወጪ መሸፈኛ፣ $100 ሺህ ዶላሩ ለምትማርበት ትምህርት ቤት፣ $50 ሺህ ዶላሩ ደግሞ በቅርብ ስትረዳትና በውድድሩ ስታበረታታት ለነበረችው አስተማሪዋ የሚሰጥ ነው። ይህ ለትምህርት ቤቷ ትልቅ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረ ማርያም ታስረዳለች።

ዘንድሮ አስራ ሁለተኛ ክፍልን አጠናቃ በመጪው አመት ወደ ዩቨርስቲ የምትገባው ማሪያም በሙዚቃና በስዕልም የተካነች ናት። የዚህ ስኬቷ ዋና ሚስጥር ግን ከጀርባዋ ሆነው ድጋፍ የሚያደርጉላት ወላጆቿ መሆናቸውን ትገልፃለች።

የማሪያም እናት ወይዘሮ መርሃዊት እዮብ የልጇን ማሸነፍ ስትሰማ የተሰማትን ስሜት ለመግለፅ ቃላት ያጥረኛል ትላለች።

ሙሉ ጊዜዋን ማሪያምንና ሌሎች ሁለት የ 15 አመትና የ 3 አመት ልጆቿን ለማሳደግ እንደሰጠች የምትናገረው መርሃዊት፣ ማሪያም ከህፃንነቷ ጀምሮ የትምህርትና የማንበብ ፍቅር እንዲኖራት መፅሀፎችን በመግዛትና በማንበብ ታበረታታት ነበር። ለልጆች ስኬት ትልቁ ነገርም ወላጆች ግዜአቸውን መስጠታቸው ነው ስትል ትመክራለች።

ማሪያም በዚህ ውድድር ስታሸንፍ የመጀመሪያ ካናዳዊ መሆኗን ተከትሎ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጀቲን ትሩዶ አኩርተሽናል የሚል መልእክት በትዊተር አማካኝነት አስተላልፈውላታል። ለማርያም ይህና ከመላው አለም የሚደርሷት የደስታ መግለጫዎች ካሰበችው በላይ እንደሆነ በደስታ ትናገራለች።

ማሪያም ባገኘችው የሽልማት ገንዘብ አሜሪካን አገር ባለ ዩንቨርስቲ ውስጥ ፊዚክስ ማጥናትና ትልቅ ቦታ መድረስ እንደምትፈልግ ነግራናለች።

XS
SM
MD
LG