በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የምስጋናና የድጋፍ ዝግጅት ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል


ለኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የምስጋናና የድጋፍ ዝግጅት ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:16 0:00

የኢትዮጵያ መንግስት ህግ የማስከበር ዘመቻ ያለውንና በትግራይ ክልል ከህወሃት ጋር ሲያካሄድ የቆየውን ውጊያ በድል ማጠናቀቁን መግለፁን ተከትሎ፣ በእርምጃው ላይ ለተሳተፉ አካላት የተዘጋጀ ልዩ የምስጋና እና የድጋፍ ስነስርዐት ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል። አንጋፋው ድምፃዊ መሀሙድ አህመድን ጨምሮ በርካታ ድምፃውያን በዝግጅቱ ላይ እንደሚገኙም አዘጋጆቹ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ መንግስታቸው በትግራይ ክልል ሲያካሂድ ቆየ ያሉትን ህግን የማስከበር ዘመቻ መጠናቀቁን የገለፁት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ነበር።

ይህን ተከትሎ በአሜሪካን አገር የሚገኙት 'ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዲሲ ግብረ ሃይል' እና 'አለም አቀፍ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት' የፀሎትና የሙዚቃ ዝግጅቶችን ያካተተ ልዩ የምስጋናና የድጋፍ ዝግጅት በጋራ አዘጋጅተዋል።

የዲያስፖራ ምክርቤቱ አባልና የዝግጅቱ የሚዲያ ሀላፊ የሆኑት ወይዘሮ ልደት ሙለታ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት የዛሬው ስነስርዓት የተዘጋጀው የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ጨምሮ በህግ ማስከበር ዘመቻው ላይ ለተሳተፉ አካላት ምስጋና ለማቅረብና ኢትዮጵያ ውስጥ ለተጎዱና ለተሰደዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለማሰባሰብ ነው።

በህወሃትና በፌደራሉ መንግስት መሃከል በተካሄድው ወደ አንድ ወር ገደማ የፈጀ ጦርነት ወቅት፣ ህዝቡ በጭንቀት ውስጥ ቆይቶ ነበር ያሉት ወይዘሮ ልደት በዛሬው እለት የተዘጋጀው ዝግጅት ከዚህ በኃላ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ብሄሮች በእኩልነት የሚከበሩበት ለውጥ የመጣል የሚል ተስፋ ማንፀባረቂያ መሆኑንም ገልፀዋል።

ወይዘሮ ልደት ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ ለሚታዩ ችግሮች በውጪ የሚኖረው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ። የድጋፍ ዝግጅቱም የዳያስፖራው ማህበረሰብ ከዚህ አይነት ድርጊት እንዲቆጠብ መልእክት ማስተላለፊያ ነውም ይላሉ።

አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደሚፈፀሙ፣ ሰዎች እንደሚገደሉና እንደሚፈናቀሉ የሚናገሩት ወይዘሮ ልደት መንግስት በትግራይ ክልል አሳክቶታል የሚሉት ህግ የማስከበር ዘመቻ በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች ጅምር መሆን አለበት ይላሉ።

በዛሬው እለት የሚደረገው የድጋፍ ስነስርዓት ሜዳ ላይ እንደሚሆንና በዝግጅቱ ላይ የሚታደሙ ሰዎች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ ማስክ በማድረግና ርቀታቸውን በመጠበቅ እንደሚታደሙ ወይዘሮ ልደት አስረድተዋል። በቀጣይም በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወጎኖች ተከታታይ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች እንደሚዘጋጁ ተናግረዋል።
XS
SM
MD
LG