ዮሀንስ ሞላ የስነ-ፅሁፍ ባለሙያና በማህበራዊ ድህረ-ገፆች ላይ በሚነሱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሀሳቡን በመግለፅ የረጅም ግዜ ተሳታፊ ነው። ከሰሞኑ ግን ዩሀንስ ማህበራዊ ድህረ-ገፆች ላይ የሚታየው ሀሳብን መግለፅ ሳይሆን የጥላቻ መረጃዎችን ማስተላለፍና ህብረተሰቡን እርስ በእርስ የሚያጋጩ መልዕክቶች ናቸው ይላል።
ባለፈው ሳምንት የታዋቂው ኦሮምኛ ድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎት ሀገሪቱ ውስጥ ሁከትን ለመቀስቀስና ጥላቻን ለማሰራጨት ይውላል በሚል ስጋት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ አድርጏል። ይህን እርምጃ የተቃወሙ ከ 40 በላይ የሚሆኑ አህጉራዊና አለምዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ኪፕ ኢት ኦን (ይከፈት) የሚል ጥምረት ፈጥረው መንግስት የወሰደው እርምጃ መሰረታዊ የሆነውን መረጃ የማግኘት መብት የሚጥስ ነው ሲሉ የጋራ ጥሪ አሰምተዋል።
የጥምረቱ አባል የሆነው አክሰስ ናው የተሰኘና፣ ተቀማጭነቱን በኬንያ፣ ናይሮቢ ያደረገ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅት ከፍተኛ የፖሊሲ አስተባባሪ የሆኑት ብርሃን ታዬ መንግስት ኢንተርኔት ለመዘጋቱ ያቀረበው በኢንተርኔት ሊፈጠር የሚችል ያለመረጋጋት ስጋት ተጨባጭ አይደለም ይላሉ።
ወይዘሮ ብርሃን አክለው፣ መንግስት እንደሚለው በኢንተርኔት አማካኝነት ሊደርስ የሚችል ጥፋት ቢኖር እንኯን ኢንተርኔቱን መዝጋት መፍትሄ አይሆንም ሲሉም ይከራከራሉ።
ሰዎች ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ የሚያምነው ዩሀንስ፣ በአሁኑ ወቅት ግን በተለይ በማህበራዊ ድህረ-ገፆች ላይ የሚታየው ሀሳብን መግለፅ ሳይሆን የጥላቻ መረጃዎችን ማስተላለፍ በመሆኑ መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቇረጡ ተገቢ ነው ብሎ ያምናል።
በአሜሪካን አገር የሚገኘው ሀምሊን ዩንቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑትና በተለይ በኢንተርኔትና ሚህበራዊ ሚድያዎች ዙሪያ ሰፊ ጥናቶችን ያካሄዱት እንዳልካቸው ጫላ፣ በአሁኑ ወቅት ኢንተርኔትን መዝጋት የመረጃ ነፃነትን ከመገደብ ባሻገር፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችና አገርን በመምራት ረገድ ውስብስብ ችግሮችን ሊፈጥር እንደሚችል ገልፀው፣ እንደ ህንድ ያሉ የተለያዩ ሀገራት ሰፊ የሆነ የሀሰትና የጥላቻ መረጃዎች ስርጭት በሚያጋጥማቸው ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የማህበራዊ ቀውስን ለመግታትና የደህንነት ችግርን ለማስቆም ኢንተርኔትን መዝጋት አማራጭ ተደርጎ እንደሚወሰድ ያስረዳሉ።
መንግስት ዜጎችን ለማፈን ኢንተርኔትን እንደፈለገ እንዳይዘጋና ተጠያቂነት እንዲኖረው የህግ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ተቋማት የተደራጁ መሆን እንዳለባቸውም አቶ እንዳልካቸው ያሳስባሉ።
የድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን መሞት ተከትሎ በተነሱ ተቃውሞዎች እስካሁን 166 ሰዎች መገደላቸውን የመንግስት ሀላፊዎች አስታውቀዋል። በሀገሪቱ ያለው ፀጥታ ተመልሶ ከተረጋጋ በዚህ ሳምንት ኢንተርኔት ተመልሶ ሊከፈት እንደሚችል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ቢሌኔ ስዩም ባለፈው ሳምንት ገልፀው ነበር።