የአሜሪካ ድምፅ፡ ድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ባለፈው ሳምንት መገደሉ ከተነገረ በኃላ የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገሪቱ ውስጥ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። እነዚህን እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ሂዩማንራይትስ ዎች እንዴት ይመለከታቸዋል?
ላቲሺያ፡ በመጀመሪያ ደረጃ ኢንተርኔትን ሙሉ ለሙሉ መዘጋቱ ቤተሰብ እርስ በእርስ እንዳይገናኝ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ችግሮችን ፈጥሯል። በተለይ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ተቃውሞዎችና ረብሻዎች በሚካሄዱበት ወቅት ሰዎች መረጃን ማግኘት አለባቸው። በኢትዮጵያ በውይይት መፈታት ያለባቸው ተገቢ የሆኑ ቅሬታዎች እየቀረቡ ነው። ስለዚህ መንግስት ትክክለኛውን መረጃ በወቅቱ ለሰዎች መስጠት መቻል አለበት። ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ያናገርናቸው ሰዎች፣ ኢንተርኔት መዘጋቱና መረጃ አለመኖሩ ለግምታዊ አስተሳሰቦችና ለተዛቡ መረጃዎች እንዳጋለጣቸው ነግረውናል። ስለዚህ መንግስት የዘጋውን ኢንትርኔት ባስቸኳይ መክፈት ይኖርበታል።
የአሜሪካ ድምፅ፡ እርግጥ ነው ማንኛውም ሰው መረጃን የማግኘትም ኾነ ሃሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብት አለው። ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎቱን ለማቋረጥ የተገደደው የጥላቻ፣ የሁከትና የግድያ ቅስቀሳ መጠቀሚያ በመሆኑ ነው ብሏል። በእርግጥም እንደምናየው በተለያዩ የማኅበራዊ ድህረገፆች ላይ የጥላቻ ንግግሮች፣ ኅብረተሰቡን እርስ በእርስ የሚያጋጩ መልዕክቶች ይሰራጫሉ። ያን ተከትሎም በሀገር ውስጥ ሰዎች ማንነታቸው ላይ መሰረት ያደረገ ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን ከጥቃት የተረፉት ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል። ኢንትርኔት በዚህ መልኩ ለጥፋት ሲውል መንግሥት ምን ዐይነት እርምጃ መውሰድ ነበረበት?
ላቲሺያ፡ መረጃ በየትኛውም መንገድ ቢሆን መውጣቱ አይቀርም። ነገር ግን እየሆነ ያለው ትክክለኛና የተጣራ መረጃ ማግኘትን አዳጋች እንዲሆን ማድረግ ነው። መረጃን በማጣራት ረገድ መንግሥትም የድህረ-ገፅ ድርጅቶችም የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። በተለይ በኢንተርኔት ዙሪያ ያሉ ባለሙያዎች ችግር ያለባቸውና ግጭት የሚያነሳሱ መረጃዎች ሪፖርት እንዲደረጉ የማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው። ኅብረተሰቡም ቢሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ መሆን አለበት። ነገር ግን አሁንም ኢንተርኔት ባለመኖሩ ይህን ሀላፊነቱን መወጣት አይችልም። ችግር ያለባቸውን መረጃዎች ስናጣራ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችንም ጠቅሎ በሚያጠፋ መልኩ መሆን የለበትም።
የአሜሪካ ድምፅ፡ የጥላቻ ንግግሮች ወይም የሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ራስምታት የሆነው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ጭምር ነው። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ያላደጉ ሀገራትና፣ ህብረተሰብን ሙሉ ለሙሉ ከጥቃት መጠበቅ የሚችል የተጠናከሩ የሕግ ተቋሟት የሌላቸው ሀገሮች፣ ኢንተርኔትን ሳያቋርጡ በሕዝባቸው ደህንነት ላይ የሚነጣጠሩ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመዋጋት የሚችሉባቸው መንግዶች ምንድን ናቸው?
ላቲሺያ፡ በመጀመሪያ አንድነትን የሚፃረሩ ንግግሮችን ከሚያደርጉ የመንግሥት አካላት ጀምሮ ያልተገቡ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ የተለያዩ መንገዶችን ለማስቆም ኅብረተሰቡ መካከል ሆኖ ይህን የሚከታተል ጠንካራና የተሳሰረ የሲቪክ ማህበረሰብ መገንባት አለበት። ይህን በማስቆም ረገድ ሌላው ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው ደግሞ እንደፌስቡክ ያሉ ኩባንያዎች ናቸው። ፌስቡክ ሀገር ውስጥ ያለውን ሁኔታ የሚከታተሉና የሚረዱ፣ አመፅ የሚያነሳሱ መልእክቶችን ሪፖርት የሚያደርጉ ሰዎች ሊኖሩት ይገባል።
የአሜሪካ ድምፅ፡ ሌላው በዚህ ወቅት መንግሥት የወሰደው እርምጃ በሀገር ውስጥ ሆነው ይሰሩ የነበሩ ነገር ግን በሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ጊዜ የነበረውን ዓይነት ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ የጥላቻ ንግግሮችን ያሰራጩ ነበር ያላቸውን የሚዲያ ተቋማት መዝጋት ነው። የናንተ ተቋም በአጠቃላዩ የሚዲያ ተቋማትመዘጋታቸውን ይቃወማል። ነገር ግን መንግስት የጥቃት መሳሪያ ሆነዋል ያላቸውን ጣቢያዎች መዝጋቱን እንዴት ታዩታላችሁ?
ላቲሺያ፡ ከመንግሥት ነፃ የሆኑ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ሞያው የሚጠብቅባቸውን የጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባርና ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለባቸው ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ በተለይ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አለመግባባቶች ባሉበት በአሁኑ ወቅት፣ ፀብን የሚያነሳሱ መልዕክቶችን ለሚያስተላልፉ ሰዎች የአየር ሰዓት መስጠት የለባቸውም። ነፃ ሚዲያ ቢሆኑም፣ እነሱም የሚሠሩት በተመሳሳይ ያልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ ሞያዊ ኃላፊነት አለባቸው።
የአሜሪካ ድምፅ፡ ስለዚህ መንግስት እደዚህ አይነት የጥላቻ ንግግርንና ፀብ የሚያጭሩ መልእክቶችን የሚያስተላልፉ የሚዲያ ተቋማትን መዝጋቱ ትክክል ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?
ላቲሺያ፡ አሁን ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ይከብደኛል ምክንያቱም ኢንተርኔት በመዘጋቱ ምክንያት ምን እንደተባለ፣ ምን ዓይነት መልዕክት እንደተላለፈ በትክክል መረዳት አልቻልንም። ነገር ግን እንደዚህ ዐይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲፈጠሩም እንኳን በአንድ ጊዜ ሚዲያዎቹን ከመዝጋትና ጋዜጠኞችን ከማሰር ይልቅ መንግሥት ነገሩን በተለየ መልኩ ሊያስተናግድባቸው የሚችሉ ሌሎች መንገዶች ሊኖሩ ይገባል።
የአሜሪካ ድምፅ፡ በኢትዮጵያ አለመረጋጋት ከተፈጠረበት ባለፈው ሳምንት አንስቶ በኦሮምያ ክልል ውስጥ ያልታወቁ ቡድኖች በሔርና ኃይማኖትን መሰረት አድርገው ጥቃት ማድረሳቸው፣ ከ177 በላይ ሰዎች መገደላቸውና ንብረት መውደሙ እየተዘገበ ነው። ሂዩማን ራይትስ ዎች መንግስት ለተቃውሞ ሰልፍ በወጡ ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረሱን አውግዞ መግለጫ ቢያወጣም፣ ስለነዚህ ግድያዎች ግን እስካሁን ምንም አላለምና ምላሻችሁ ምንድን ነው?
ላቲሺያ፡ ኦሮሚያ ውስጥ ኦሮሞ ባልሆኑ ግለሰቦች ንብረት ላይ የደረሰውን ንብረት ስንመዘግብ ቆይተናል። አሁን በተጨማሪ በአርሲና ባሌ ዞኖች ደረሱ ስለሚባሉት ግድያዎች እያጣራን ነው። ባለፈው ዓመት ጥቅምት ላይም ተመሳሳይ ከተሞች ውስጥ በሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት መድረሱን መዝግበን ነበር። ነገር ግን አሁንም የኢንተርኔት መዘጋት የማጣራት ስራችንን እያጓተተው ነው።
የአሜሪካ ድምፅ፡ ግን እኮ እነዚህ ጥቃቶችና ግድያዎች እየተፈፀሙ ቀድሞውንም የኢንተርኔት አገልግሎት በስፋት በማይገኝባቸው የገጠር ከተሞች ውስጥ ነው? ስለዚህ እንደነዚህ ዓይነት ቦታዎች ላይ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አትመዘግቡም ማለት ነው ወይስ መረጃ በምን መልኩ ነው የምትሰበስቡት?
ላቲሺያ፡ እያወራን ያለነው በተለያዩ የገጠር ከተማዎች ላይ ስለተፈፀሙ ጥቃቶች ነው። መጀመሪያ የት ምን እንደተፈጠረ ማወቅ አለብን፣ ከዛ ስልኮች እንደውላለን። አሁን ግን ቀጥታ ስልክ መስመሮችንም ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው።
የአሜሪካ ድምፅ፡ ግን በነዚህ ቦታዎች ላይ በመንግሥት ታጣቂዎች ስለደረሱ ጥቃቶች መግለጫ አውጥታችኃል። መንግስትን ብቻ የሚከሱ መግለጫዎችን እያወጣችሁ በሌሎች ቡድኖች የሚፈፀሙ ጥቃቶች ላይ ዝም ማለታችሁ ሂዩማን ራይትስ ዎች ወገንተኛ ሆኖ እንዲታይ አያደርገውም?
ላቲሺያ፡ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ በዋናነት የመንግስት ኃላፊነት ነው። መንግሥት ወንጀል እንዳይሠራ፣ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ቁጥራቸው አናሳ የሆኑ ብሄሮች ጥቃት እንዳይደርስባቸው፣ ንብረታቸው እንዳይጠፋ ከለላ መስጠት አለበት። እኛ እንደሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት፣ በሰብዓዊ መብት መርሆች መሰረት ነው የምንመራው፣ ያ ደግሞ መንግስትን ኃላፊ አርጎ የሚጠይቅ ነው። ደግሜ ማስታወስ የምፈልገው፣ ባለፈው ጥቅምት መንግስት ከበቂ በላይ ሀይል ተጠቅሞ በአምቦ ያደረሰውን የመብት ጥሰትና በብሔሮች መካከል በነበረ ግጭት በዶዶላ የተፈፀሙ ወንጀሎችንና የንብረት ውድመቶችን መዝግበናል።
የአሜሪካ ድምፅ፡ ሚስስ ቤይደር ጊዜዎትን ሰጥተው ለጥያቄዎቼ ምላሽ ስለሰጡንና ሰለነበረን ቆይታ እናአሰግናለች።
ላቲሺያ፡እኔም አመሰግናለሁ
----
(የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ስመኝሽ የቆየ ከሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሺያ ባይደር ጋር ያደረገችውን ቆይታ በድምፅ ለመከታተል የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ይጫኑ)