የ 18 አመት ወጣቱ ደጀኔ ደገፋ ካደገበት የቢሾፍቱ ገጠራማ አካባቢ ለቆ ሲወጣ እቅዱ ከስራ አጥነት ለመላቀቅና በደቡብ አፍሪካ ስራ አግኝቶ የሚያገኘውን ገንዘብ ለቤተሰቦቹ ለመላክ ነበር። በምትኩ ግን ያጋጠመው ህይወቱን ሊያሳጣው ነበር።
ደጀኔ መጋቢት 15 ቀን በሞዛምቢክ ውስጥ ለቀናት አየር በሌለው የእቃ መጫኛ ኮንቴይነር ውስጥ ተቆልፎባቸው ከሞት ከተረፉት 14 ወጣት ኢትዮጵያውያን መሀል አንዱ ነው። በህገወጥ አዘዋዋሪዎች አመቻችነት ከእነሱ ጋር አብረው ሲጏዙ የነበሩ 64 ስደተኞች ኮንቴይነሩ ውስጥ ህይወታቸው አልፏል።
ደጀኔ ለቪኦኤ ሲናገር የህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ ደቡብ አፍሪካ እንዲያደርሱት 200 ሺህ ብር ከፍሏል። ሞዛምቢክ ከመድረሱ በፊተም ለ ስድስት ወራት ያክል ያለምግብና ያለውሀ፣ በጫካ ውስጠ በእግር ተጉዟል። አገሬ በመመለሴ በጣም ደስተኛ ነኝ የሚለው ደጀኔ፣ አሁን ያለው ምርጫ ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሶ ሊያገኘው በሚችለው እርሻ ስራ ላይ መሰማራት እንደሆነ ያስረዳል።
አስራ አንዱ ስደተኞች በአዲስ አበባ የኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪዮች ለይቶ ማቆያ ስፍራ ለሁለት ሳምንት ተለይተው ከተቀመጡ በኃላ፣ አርብ እለት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርግጏል። ከተረፉት መሀል ሶስቱ ሞዛምቢክ ውስጥ ባለ ሆስፒታል እርዳታ እየተደረገላቸው ሳለ ማምለጣቸውን የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት አስታውቕል።
ከኢትዮጵያ ጉዞ የጀመሩት 78 ወጣቶች ሞዛምቢክ ውስጥ ያለ ቴቴ የተባለ ከተማ ከመድረሳቸው በፊት 4 ሺህ ኪሎሜትር ያክል በእግርና በጭነት መኪና እያፈራረቁ ተጉዘዋል። ቴቴ ላይ የሚገኝ የፍተሻ ጣቢያ አካባቢ ተዘግቶባቸው የቆዩት ስደተኞች አየር ሲያጥራቸው የጭነት መኪናውን በመደብደብ የእርዳታ ጥሪ ማሰማታቸውን ከሞት ተራፊዎቹ ይናገራሉ።
የ19 አመቱ ሙሉጌታ ኤርደሎ የሞዛምቢክ ባለስልጣናት ከጭነት መኪናው ውስጥ ሲያወጡት እራሱን አያውቅም ነበር።
በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን ለማናገር የተደረገው ጥረት ባይሳካም የደረሰውን አደጋ ለማጣራት የኢትዮጵያና የሞዛምቢክ ባለስልጣናት በቅንጅት እየሰሩ እንደሆነ በኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት ፕሮግራም አስተባባሪ ሳራ ባሻ ያስረዳሉ።
የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በህገወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡት ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው እድሜያቸው ከ 15 እስከ 35 ይሆናል የሚሉት ሳራ፣ ይሄን ህገወጥ ዝውውር ለማስቆም የተለያዩ ባለስልጣናት እየሰሩ ቢሆንም ገና ብዙ የሚቀር ስራ አለ ይላሉ።
ወይዘሮ ባሻ አክለውም ከመቶ አስር ሚሊዮን በላይ የህዝብ ቁጥር ባለበት ታዳጊ አገር ላይ ስራ አጥነት ቁጥር መብዛት፣ የህገወጥ አዘዋዋሪዎችን መንገድ ለማጥፋት የሚሰራውን ስራ አዳጋች አርጎታል ብለዋል።