ዋሽንግተን ዲሲ —
ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ በቢሊየኖች የሚቆጠር ህዝብ ከቤት እንዲውል ምክንያት ውሏል። ኢትዮጵያዊያንም ከዚህ የዓለም አዲስ ልምድ አልተነጠሉም። በርካቶች ከእንቅስቃሴዎች ተቆጥበው፣ አስጨናቂዎቹን ቀናት እየገፉ ይገኛሉ።
እንዲህ ያለውን ጊዜ ለመልካም ፍሬ ለማብቃት የወጠኑት የብሄራዊ ቤተ-መጽሃፍት ኤጀንሲ እና ዋና መቀመጫውን በዮናይትድ ስቴትስ ያደረገው ፀሃይ አሳታሚ ድርጅት ግን ከአንድ ዘመቻ ጋር ብቅ ብለዋል።
ዘመቻው « እናንብብ ፤እናብብ» ይሰኛል። በተለያዩ ዘርፎች ዕውቅናን ያገኙ ሰዎች እየተሳተፉበት በሚገኘው በዚህ ዘመቻ ፣መጽሃፍት በቴሌቭዥን እና ራዲዮ ጣቢያዎች እየተተረኩ፣ የንባብን ባህል በቀጣዩ ትውልድ ዘንድ ያሰርጻሉ የተባሉ ተግባሮችም እየተከናኑ ይገኛሉ።
ስለ ዘመቻው ዝርዝር ጉዳዮች ለማውቅ እንዲሁም ተያያዥ ንባብ -ተኮር ሀሳቦችም ይነሱ ዘንድ የፀሃይ አሳታሚ ድርጅት ባለቤት እና ስራ አስኪያጅ ከሆኑት አቶ ኤልያስ ወንድሙ ጋር ሀብታሙ ስዩም አጭር ቆይታ አድርጓል።