በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መልካም ስም የተከተለው የኤርሚያስ አስገዶም(ኒፕሲ ሃስል) ሽኝት


መልካም ስም የተከተለው የኤርሚያስ አስገዶም(ኒፕሲ ሃስል) ሽኝት
መልካም ስም የተከተለው የኤርሚያስ አስገዶም(ኒፕሲ ሃስል) ሽኝት

ኒፕሲ ሃስል ወይም ኤርሚያስ አስገዶም፣ ከሙዚቃ ሞያው በላይ በጎ ተግባሩ በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅኖ እንዳሳደረባቸው ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በተዘጋጀው የሻማ ማብራት ሥነ - ሥርዓት ላይ የታደሙ ወጣቶች ይናገራሉ

ባለፈው ሳምንት እሁድ ሎስ-አንጀለስ ውስጥ በስድስት ጥይት የተገደለው ኤርትራ - አሜሪካዊው የሙዚቃ ሰው ኒፕሲ ሃስል ፣በወጣትነቱ ያከናወነው በጎ ተግባር በሚሊዮን ወጣቶች ልብ ውስጥ የብርሃን አሻራ መተውን በመግለፅ እማኝነታቸው ሰጥተውለታል።

“ሰው ከመሆን ውጪ ያሉት ነገሮች ሁሉ ለእርሱ ቦታ አልነበራቸውም!” ሲሉ የዘከሩት ወጣቶች ፣ሐሙስ መጋቢት 26.2011 ምሽት ዋሽንግተን ዲሲ ማልኮም ኤክስ መናፈሻ ውስጥ በመገናኘትና የሻማ ማብራት ሥነ- ሥርዓት በማዘጋጀት “ነፍስህ በሰላም ትረፍ” ሲሉ ፀልየውለታል።

ኤርሚያስ በኢኮኖሚ ደከም ያሉ ማህበረሰቦችን ከፍ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን በመወጠን ፣ማህበረሰቡ ጤናማ ኑሮ እንዲኖር የሚያስችሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በመገንባት፣የጤናማ አመጋገብ መርሃ ግብሮችን በማስተባበር በመልካም ስሙ ይነሳል፡፡

ከአፍሪቃ ወደ ዮናይትድ ስቴትስ ከሄዱ ወላጆች የተወለዱ ፣ በተለይም የዘር ግንዳቸው ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የሆነ የመጀመሪያ ትውልድ አባላት አሜሪካዊያን ወጣቶች - “ኒፕሲ ሃስል በስራው ብዙ አስተምሮናል::” ይላሉ።

ረድኤት በፍቃዱ አንዷ ነች።

መልካም ስም የተከተለው የኤርሚያስ አስገዶም(ኒፕሲ ሃስል) ሽኝት
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:30 0:00

(ካሜራ አቢሰን- Abby Sun)

ረድኤት እንደምትለው፤ ኒፕሲ ከታወቀበት የራፕ ሙዚቃ ሥራው በላይ ትልቁን ዋጋ የምትሰጠው በሚኖርበት አካባቢ አብረውት ላደጉ ጓደኞቹና ማህብረሰብቡ ላበረከተው አስተዋጾ ነው። በተጨማሪም የእርሱን ስራዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ለሚከታተሉ ሁሉ የሚያደርጋቸው አነቃቂ ንግግሮችና፣ከንግግር ለፉ ተግባሮቹ አሁን ላለው ትውልድ ምሳሌ ነበር መሆኑን ትጠቅሳለች። እርሷ ኢትዮጵያዊ ብትሆንም ኤትራዊ በመሆኑ አንድ “ደማችን አንድ ነው” የሚል ስሜት እንደነበራት ትናገራለች።

“ተፅዕኖና ለውጥ ፈጣሪ ነው ። እኔን በተለይም የመጀመሪያ ትውልድ ሐበሾች ላይ መልካም ተፅኖ ፈጥሯል። የሚፈልገውን አሳክቷል። በአሜሪካ ውስጥም ትልቅ ተፅኖ ለመፍጠር ችሏል” ስትልም ታክላለች፡፡

ቤተሰቦቹ ከሶማሌ ላንድ የሆኑት አብደላ በኒፕሲ ሃስል መታሰቢያ ስነስርዓት ላይ ያገኘነው ሌላ ወጣት ነው፡፡ያኔ ገና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ጀምሮ በሙዚቃ ስራው ይመሰጥ እንደነበር የሚናገርለትን ኒፕሲ ሃስል ሲያስብ በማህበረሰቡ ውስጥ የዘራውን መነቃቃት ሊዘነጋ እንደማይችል ይናገራል፣“የማኅበረሰቡ ትልቅ አባል ነበር ሕዝቦችን ለዓመታት የቆየውን ጉዳት እንዴት መስበር እንዳለባቸው አስተምሯል፣ የህንፃዎች ባለቤት እንዴት መሆን እንደሚቻል፣ የገንዘብ ብክነት የመሰሉ ትልቅ የሕይወት ትምሕርቶችን እሱን ለመሰሉ ወጣቶች ሰጥቷል” በማለት በ33 ዓመቱ የተቀጠፈውን የሙዚቃ ሰው ያስታውሳል፡፡

ኒፕሲ ሃስል ባለፈው የአውሮፓ ዓመት ለገበያ ያቀረበው ‹‹ቪክትሪ ላፕ›› አልበም በሙዚቃው ዓለም ትልቅ ስም ለሚሰጠው የግራሚ ሽልማት ከመታጨቱ በተጨማሪ በቢልቦርድ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ምርጥ 200 ሙዚቃዎች ዝርዝር ላይ 4ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡ከሙዚቃው ጎን ለጎን ተወልዶ ያደገበትን በኢኮኖሚ ደከም ያለ የክሬንሾ መንደር ለመለወጥ የተለያዩ ስራዎችን ይሰራ ነበር፡፡የመገደሉ ዜና የተሰማው ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራዎች የሚሰሩበትን ሁኔታ በሚመክርበት ዋዜማ ስለመሆኑም ተዘግቧል፡፡እንዲህ እንዲህ ያለው ተሻጋሪ ምግባሩ ይመስላል ቤቲ ብሩክን የመሰሉ አድናቂዎችን ያበረከተለት፡፡ቤቲ የኒፕሲ ምግባር ተቀጥራ በምትሰራበት ስራ የማህበረሰብ ህይወትን የምትለውጥበትን ዕድል እንድትመረምር እንዳገዛት ስትመሰክር፤ “እኔ በአንድ ትምሕርት ቤት ውስጥ በስነ ልቦና አማካሪነት እሰራለሁ፡፡ ለሀበሾችም ሆነ ለሌሎች ደጀን መሆን እፈልጋለሁ። ሕዝባቸውንና ባህላቸውን እንዲደግፉ አበረታታቸዋለሁ። ሂዱ ገንዘብ አፍሩ ሆኖም አገራችሁ ተመለሱና ቤተሰቦቻችሁን ተንከባከቡ እላቸዋለሁ።” ትላለች፡፡

በስነ- ስርዓቱ ላይ ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የተውጣቱ ወጣቶች ተገኝተዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ቀለም እና ዘር ሳይለዩ በአንድ ቦታ ተሰብስበው ፣ሻማ እያበሩ እና ጸሎት እያሰሙ ፤በወጣትነቱ የተቀጠፈውን የሙዚቃ ሰው መዘከራቸውን ያስተዋለችው ናፍቃን ግደይ የምትመለከተውን ‹‹አብሮነት›› ‹‹የኒፕሲ ውጤት ነው!›› ትለዋለች፣“ በዚህ ያሉት ከተለያዩ ማኅበረሰቦች የመጡ ሰዎች ኒፕሲ በዓለም ላይ የብዙ ሺህ ሰዎችን ሕይወት እንዴት እንደነካ የሚያሳዩ ናቸው። ስለሆነም ኒፕሲ ልዩ ሰው ነበር። የንግድ ሰው፣ የኪነጥበብ ሰው፣የለውጥ አራማጅ፣ ገጣሚ የነበረው ኒፕሲ ብዙዎችን አነቃቅቷል የኤርትራና የአፍሪካ ባህል እንዲጎላ አስተዋፆ አበርክቷል” ስትል ስሜቷን ለአሜሪካ ድምጽ አጋርታለች፡፡

በወጣቶች ዕውቅና የተሰጠውን የኤርሚያስ አስገዶም መልካም ስራ ያጤኑ የሚመስሉ እንደራሴ ካረን ባስን የመሰሉ የሎስ አንጀለስ ከተማ ምክር ቤት አባላት ፣በቀጣይ ሳምንት በምክር ቤቱ ቀርበው ኤርሚያስ ስሙ በምክር ቤቱ መዝገብ ላይ እንዲሰፍር እንደሚጠይቁ በማህበራዊ መገናኛ አውታራቸው ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG