Reliefweb የተባለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድረ-ገጽ ኢትዮጵያ ውስጥ በክረምቱ ወራት በአንዳንድ የሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ የተከሰተው የዝናብ እጥረት የቁም ከብቶች ሞትን እንዳስከተለ ጠቁሟል።
ዝናብ በመዘግየቱና በአጠቃላይም በቂ ዝናብ ባለመገኘቱ በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በደቡባዊ ኤርትራና በምስራቅ ሱዳን የድርቅ ሁኔታ እንዳስከተለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድረ-ገጽ ጠቅሷል።
በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በሱዳን ድንበሮች ዝናብ እየጨመረ እንደሚሄድ ስለሚጠበቅ ሁኔታዎች ሊሻሻሉ እንደሚችሉ ድረ ገጹ ዘግቧል። ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ የዝናቡ ሁኔታ እየተሻሽለ ቢሆንም ዝናቡ እጅግ ዘግይቶ በመምጣቱ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ማዕከልና በምስራቃዊ ክፍሎች የቁም ከብት ሞትን አስከትሏል።
በቶጎ፣ በጋናና ቤኒን ደቡባዊ ክፍሎችም፣ በዝናብ እጥረት ምክንያት በሰብሎች ላይ ጉዳት መድረሱን በምዕራብና በሰሜን ማዕከላዊ ናይጀርያም እንደዚሁ የድርቅ ሁኔታ ማስከተሉን፣ Reliefweb ድረ-ገጽ አውስቷል።
በሌላ ዜና ደግሞ የፖልዮ ማለት የህጻናት ልምሻ በሽታ በአንድ አመት ውስጥ በማናቸውም የአፍሪቃ ሀገሮች አለመታየቱ ትልቅ ስኬት እንደሆነ The New York Times ጋዜጣ ድረ-ገጽ ዘግቧል።
ከቅርብ አመታት ወዲህ ፖልዮ ወደ መጥፋት የተጠጋ ይመስልና በተለይም ናይጀርያ ውስጥ ተመልሶ ሲስፋፋ ቆይቷል። ባለስልጣኖች ታድያ ይህን ችግር ለመፍታት የፖልዮ ክትባትንና ክትትሉን በሚመለከት አዲስ ዘዴ ቀየሱ። ያልተከተቡትን ህጻናት ፈልጎ ለማግኘት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን አስማሩ። በአገር አቀፍ ደረጃ የእምነት መሪዎችንና የአከባቢ ሃላፊዎችን ድጋፍ ለማግኘት በሽታው የደረሰበት ሁኔታንም ለመከታተል የሚያስችሉ ማእከሎችን መሰረቱ። ውጤቱ ታድያ ግሩም ሆነ ሲል፣ The New York Times ጋዜጣ ድረ-ገጽ አስገንዝቧል። ሙሉውን ቅንብር ያድምጡ።