በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካ የፖለቲካ በዓል - ጥቅምት 27 /ኖቬምበር 6/


የአሜሪካ የፖለቲካ በዓል
የአሜሪካ የፖለቲካ በዓል
ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን በመላው ዩናይትድ ስቴትስ መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየጎረፉ ይገኛሉ - ፕሬዝዳንት ኦባማን በድጋሚ ለመምረጥ ወይንም ሚት ሮምኒን ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የአሜሪካ መሪ ለማድረግ፡፡

ውጤቱ ግን አሁንም በጉጉት የሚጠበቀው ብሔራዊው አጠቃላይ ምርጫ በመገባደድ ላይ ይገኛል፡፡ ለአንድ ዓመት ተኩል የተካሄደ የምርጫ ቅስቀሣ፤ ሦስት ፕሬዚዳንታዊና አንድ የምክትል ፕሬዚዳንት ዕጩዎቹ የግንባር ክርክር አልፈዋል፡፡ አሁን በሺሆች የሚቆጠሩ የቴሌቪዥን፣ በኋላም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የቅድመ ምርጫ ትንበያዎች ሁለቱ ዕጩ ተወዳዳረዎች እጅግ በቀረበ ልዩነት ላይ እንደሚገኙ ነው የሚጠቁሙት፡፡
በተጨማሪም እነዚህ የቅድመ ምርጫ ትንበያዎች ፕሬዚዳንት ኦባማ ጥቂት በሆኑ ለምርጫው ወሣኝ የሆኑ ስቴቶች ውስጥ በትንሽ ልዩነት እየመሩ እንደሆነ ያሣያሉ፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የምርጫ ውጤት የመጨረሻ ውጤት የሚወጣው በብሔራዊ አጠቃላይ ምርጫ ውጤት ብቻ ሣይሆን ሁለት መቶ ዓመታትን ባስቆጠረው ኢሌክቶራል ኮሌጅ እየተባለ በሚጠራው የምርጫ አሠራር ነው፡፡
በዚህ መሠረት ሃምሣዎቹም የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች በምርጫው ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ከጠቅላላው የሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ተመጣጠኝ ነው፡፡
ከአጠቃላይ 538 የኢሌክቶራል ኮሌጁ ወይም የመራጭ ውክልና ድምፆች የምርጫ ድምፅ አሸናፊ ለመሆን አንዱ ተወዳዳሪ ቢያንስ 270ውን ማግኘት ይኖርበታል፡፡

በዛሬው አጠቃላይ ምርጫ ከፕሬዝዳንታዊው ውድድር በተጨማሪ መራጮች 435 መቀመጫ ላለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ የህግ መምሪያ እንደራሴዎችን፤ እንዲሁም ከ100ው የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ መቀመጫዎች 33ቱን ይመርጣሉ፡፡ ሪፐብሊካኑ በሕግ መምሪያው ውስጥ የበላይነቱን ይዘው ሊቀጥሉ ዴሞክራቲክ ፓርቲው ደግሞ የህግ መወሰኛውን በጠባብ ብልጫ እየመሩ እንደሚቀጥሉ ተንታኞች እየተነበዩ ነው፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ መራጮች ከምርጫው ዕለት በፊት በተከፈቱት የድምፅ የመስጫ ቀናት መርኃግብር መሠረት ቀደም ብለው ምርጫቸውን አጠናቅቀዋል፡፡
በምርጫው ዕለት ድምፅ ያልሰጠው አብዛኛው መራጭ ወደ ትምህርት ቤቶች፤ አብያተ ክርስትያን እና በሌሎችም የሕዝብ አካባቢዎች በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ድምፁን ይሰጣል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ መሠረታቸው በሆነችው ኢሊኖይ ስቴት ዋና ከተማ ችካጎ ቅርብ ቀናት ተገኝተው ድምፃቸውን የሰጡ ሲሆን የምርጫውን ምሽት ማክሰኞንም እዚያው ለማሣለፍ ወስነዋል፡፡

ተቀናቃኛቸው ሮምኒም በፊት ባስተዳደሯት፤ ነገር ግን በአሁኑ ምርጫ ኦባማ በሚመሩባት በሰሜናዊቱ ማሳቹሴትስ ስቴትስ በምርጫው ዕለት ማለትም ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት ነው የመረጡት፡፡

ተቀናቃኙ ሮምኒ የምረጡኝ ዘመቻቸውን በምርጫውም ዕለት ለመቀጠል ወስነው ሲቀሰቅሱ ውለዋል፡፡ በምርጫ ቀን ዘመቻቸው ዕቅዳቸው ውስጥ የጠነከረ ትንቅንቅ በሚካሄድባትና ወሣኝ የሆነ 18 ኢሌክቶራል ድምፅ ዕጣ ፈንታ በሚወሰንባት ኦሀዮ፤ ለረጅም ግዜ ኦባማ ይመሩባታል ተብላ የታሰበችው ነገር ግን ሮምኒ አሸንፋለሁ ብለው ተስፋ በጣሉባት ፔንሲልቬንያ ስቴት ይሆናል፡፡

ፕሬዝዳንት ኦባማ የመጨረሻ ቅስቀሣቸውን በአዮዋ ባደረጉበት ወቀት ባደረጉት ንግግር አስተዳደራቸው ባለፉት ዓመታት ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ያሏቸውን ጉዳዮች ከዘረዘሩ በኋላ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡

የለውጥ ጎዟችን ይቀጥላል፤ ምክንያቱም አገራችን ቁጥሩ እየሰፋ ከሚሄደውና በብዙ ከሚታትረው ባለመካከለኛ ገቢ፤ እዛም ለመድረስ ከሚፈልጉትና ከሚለፉት ውጪ እንደማታሸንፍ እናምናለን፡፡ ትግላችን አሁንም ይቀጥላል፤ ምክንያቱም አሜሪካ ሁሌም የምታሸንፈው ሁሉም ሰው እኩል ዕድል ተሰጥቶት የተቻለውን ሲሠራ እና በአንድ ሕግ ሲመራ ነው - ብለዋል ፕሬዚዳንት ኦባማ፡፡

የአዮዋ ሕዝብ ይህን ያውቃል - አሉ ኦባማ - ይሄንኑ ነው የምናምነው፡፡ ለዚሁ ነው በ2008 የመረጣችሁኝ፤ ለዚህም ነው ድጋሚ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ለመሆን የምወዳደረው፡፡

ተቀናቃኙ ሮምኒ ደግሞ በፍሎሪዳ፣ በቨርጂንያና በኦሃዮ ካደረጉት ቅስቀሣ በኋላ በዚህ ዓመት ዘመቻቸውን በጀመሩባት በኒው ሃምፕሻየር ትናንት ሰኞ ማታ ባዘጋጁት አነቃቂ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የተዋጣለት የቢዝነስ ሰውና ፖለቲከኛ፣ እውነተኛ ለውጥ የሚያመጡት እርሣቸው እንጂ ኦባማ አይደሉም ብለዋል፡፡

የግል ሥራ አቋቁሚያለሁ፤ መርቻለሁ፡፡ ሌላ የንግድ ተቋም ከኪሣራ አውጥቼ አትራፊ አድርጌአለሁ፡፡ የሃገሪቱ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከውድቀት ወጥቶ ስኬታማ እንዲሆን አድርጌአለሁ፡፡ ክልሌን ከውድቀት ወደ ብልፅግና፤ ከሥራ አጥነት ወደ ሥራ ዕድገት፤ ሰዉን ከበዛ ታክስ ከፋይነት ወደ በረከተ ክፍያ ተቀባይነት አድርሻለሁ፡፡ ለዚህ ነው ለፕሬዝዳንትነት የምወዳደረው፡፡ ምክንያቱም ሃገራችን ዛሬ ካለችበት ሁኔታ እንዴት ማውጣት እንደምንችል አውቃለሁ፡፡ ደግሞም አደርገዋለሁ - ብለዋል ሮምኒ፡፡

የድምፅ አሰጣጡ በሁሉም የአሜሪካ ስቴቶች ውስጥ እየተካሄደ ነው፡፡

please wait

No media source currently available

0:00 0:10:00 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ
XS
SM
MD
LG