እንደ ተዘዋዋሪ የመረጃ ምንጭነት ለዓመታት ማህበራዊ መገናኛዎችን የተጠቀመው ሲሳይ ፣ እየተበራከቱ የሚገኙ ግብሮች ምቾት የሰጡት አይመስልም።
«ገነው የሚታዩት አልባሌ ተግባር የሚፈጽሙ ሰዎች ናቸው።አንዳንዴ የስድብ ውድድር ያለ እስኪመስል ድረስ ፣የከሌ ይሄንን አለች የከሌ ይሄን አለ መባባል (በርክቷል) . . . አዲስ ነገር እየለመድን ነወይ? የሚያስብል አሳፋሪ አካሄድ (እያየን) ይመስለኛል» -ሲል ይናገራል።
ንትርክ፣ ዘለፋ፣ ጩኸት የበዛባቸው የማህበራዊ ማህደሮች መብዛታቸው የሚያሳስበው ሲሳይ በአንዳንዶቹ ላይ የሚወጡትን መልዕክቶች ሲያጤን በግራ መጋባት እና አለማመን ውስጥ እንደሚገባም -የአድራጊዎችን አዕምሯዊ ጤንነት እንደሚጠራጠርም ያወሳል።
የማህበራዊ መገናኛዎች መጤ ድባብ ላይ ቅሬታ የሚያቀርበው ሲሳይ ብቻ አይደለም። ዮሐንስ ሞላን የመሰሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው አዘውትረው ሀሳቦቻቸውን የሚያጋሩ ጦማሪያንም እየተንሰራፋ የመጣው አሉታዊ አጠቃቀም ተሰምቷቸዋል።
የስድድብ እና የዘለፋ ማህደሮች ከማብዛታቸው በፊት ማህበራዊ መገናኛዎች ለመልካም የዋሉባቸው አጋጣሚዎች ለዮሐንስ የራቁ ትዝታዎች አይደሉም።ዮሐንስ ከሚጠቅሳቸው የቀደሙ ግብረ -ሰናይ እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ፣ «ደጉ ኢትዮጵያዊ» በተሰኘ ዕድሜው በአጭሩ የተቀጨ የፌስቡክ ቡድን የተከናወነ ነው።
ዓለም ደቻሳ የተባለች ኢትዮጵያዊት ሊባኖስ ውስጥ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቷን መጣቷን ተከትሎ ቡድኑ በዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ችግር ለማሰተጋባት እና ለመደጋገፍ ፌስቡክን በጊዜው መጠቀሙን ያስታውሳል።
«እኔ ራሴ ፌስቡክን ተጠቅሜ ካስተባበርኳቸው ጉዳዮች አንዱ ለአማኑዔል ሆስፒታል ቤተመሕሃፍትን ማቋቋም (አንዱ )ነው።ለቪክቶሪ መስማት የተሰናቸው ህጻናት ማዕከልም መጽሃፍትን ለማሟላት (ተንቀሳቅሰናል)። ፌስቡክን ተጠቅመን ቤተመጽሃፍቶቹ ዕውን ሆነዋል።»-ሲል ያክላል።
መሰል መደጋጋፎች ከማህበራዊ መገናኛ አውታሮች ሙሉ በሙሉ ባይጠፉም ፣ አውታሮችን ለአውዳሚ ተግባራት የሚያውሉ ቀን ተቀን መብዛታቸውን የሚጠቁሙ ጥቂት አይደሉም።
ለመሆኑ ተጠቃሚዎች በአውዳሚ የማህበራዊ መገናኛ ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ለምን ይመርጣሉ ?
የስነ -አዕምሮ ሀኪሙ ዶ/ር ዳዊት አሰፋ ጉዳዩ ከሰው ልጆች ስነ-ልቦናዊ ውቅር መነሳት እንዲታይ ይፈልጋሉ፣«የሰው ልጅ በጎም ሆነ እኩይ የሆነ የታመቀ ስሜት አለው።የእርስ በርስ መስተጋብራችን የሚመጣው ይህ ስሜት የተለያዩ የማስታረቂያ ሂደቶችን( ደረጃዎችን )ከአልፈ በኃላ ነው።የማህበራዊ ሚዲያው በጣም ነጻና በቀላሉ የሚገኝ መሆኑ ያንን የታመቀ ስሜት አውጥቶታል ማለት እንችላለን» የሚሉት ዶ/ር ዳዊት በማህበራዊ መገናናዎች የአጥፊነት ባህሪያትን የሚያሳዩ ግለሰቦችን ከአዕምሮ ህመም ጋር የማገናኘት ፍረጃ ግን ተገቢ እንዳልሆነ ይሟገታሉ። አሁን ያለው ዓለማዊ ሁኔታ ሰዎች ራሳቸውን መቆጣጠር የሚችሉበትን ስነ አዕምሯዊ ሁኔታ እየፈተነው እንደሆነ ግን ያምናሉ።
ተግባራቱ ለምን ተስፋፉ? ምንስ መደረግ አለበት? ሙሉ መሰናዶ ያዳምጡ።