ጥቅምት 29/2014 - በብዙ መቶዎች የተገመቱ ትውልደ- ኢትዮጵያዊያን ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት መናገሻ ዋይት ኃውስ ቤተመንግስት ፊት ለፊት በመገኘት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። ሰልፉ ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው አንድ ዓመት በጦርነት ውስጥ በቆየችው ኢትዮጵያ ላይ "አድርሳዋለች" የተባለውን ያልተገባ ጫና የማውገዝ፣ በጦርነቱ ህይወታቸውን ያጡትን መዘከር እና ለተፈናቀሉትም እርደታን የማሰባሰብ ዓላማ እንዳለው ከአስተባባሪዎች ሰምተናል።
ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ሰልፍ ላይ የተሳተፉት አካላት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በታዘባ መንገድ ሽፋን እየሰጡት ናቸው ያሏቸውን ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን አውግዘዋል፣ ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ወቅታዊ አቋሟን በድጋሚ እንድታጤን አሳስበዋል።
ቁጥሩ ያልታወቀ ሰው ህይወት የቀጠፈው እና በሚሊየኖች የሚቆጠሩትን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለው ጦርነት የዛሬ ዓመት በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ከተቀሰቀሰ ወዲህ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና አጋሮቹ ከትግራይ ኃይሎች ጋር የገቡበትን ግጭት አቁመው ወደ ሰላማዊ መፍትሄ ፊታቸውን ያዞሩ ዘንድ፣ ደረሱ በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ምርመራ እንዲደረግ እና ጥፈተኞችም ተጠያቂ እንዲሆኑ ስታሳሳብ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከተንሰራፋው ግጭት ጋር በተያያዘ በተለያዩ ዙሮች ለሰብዓዊ ድጋፎች የሚሆን እገዛ ያደረገችው ዩናይትድ ስቴትስ ፣ ተፋላሚ ወገኖች መሳሪያቸውን ያስቀምጡ ዘንድ ጫና እንደሚፈጥሩ የታመነባቸው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃዎችን መውሰዷ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ውስጥ ችግር በጠመንጃ አይፈታም ብላ የምታምነው አሜሪካ ፣ የተሻለ መፍትሄ ለማምጣት በማሰብ ከሰሞኑ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማንን ወደ ኢትዮጵያ የላከች ሲሆን ፣ እሳቸው በተፈላማኢ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ይደረስ ዘንድ ጥረት እንደሚያደርጉ ተነግሯል ።
ሰልፉን የተመለከተውን የቪዲዮ ዘገባ ይመልከቱ ።