ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
በውብ ሰንሰለታማ ተራሮች የተከበቡ ስፍራዎችን ማየት፣ ደኖች የሞሉት፣ ንፁህ አየር የሚነፍስበትና የወፎች ዝማሪ የበዛበትስፍራዎች ላይ ንፁህ አየር መተንፈስ፣ ተፈጥሮ በለገሰቻቸው ማራኪ ቦታዎች ላይ ከራስ ጋር የመነጋገሪያ ጊዜ ማግኘት፣ እነዚህሁሉ የድምፅ ባለሙያ የሆነውን የ 26 አመቱን ረደላ መሀምድን በየ 15 ቀኑ ከአዲስ አበባ ራቅ ወዳሉ ቦታዎች እንዲወጣምክንያት ከሚሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው።
ረደላ የእግር ጉዞ ማደረግና ከከተማ ራቅ ብሎ በመሄድ ለእራሱ ጊዜ መስጠትን የተለማመደው ከ 8 አመት በፊት ነበር። ይሄልምዱ እራሱን እንዲያዳምጥና በህይወቱ ጠንካራ እንዲሆን እንዳደረገው ይናገራል።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰዎች የሚፈሱባት የኢትዮጵያ መዲና እጅግ የበዙ ነዋሪዎቿን በበቂ ሁኔታ የምታስተናግድበትመሰረታዊ ልማት ካለማሟሟላቷ ባሻገር፣ ንፁህ አየር የሚያስተነፍሱ መናፈሻ ቦታዎች በቅጡ የላትም፣ ያሉትም በአግባቡአገልግሎት አይሰጡም። በዚህ ምክንያት ካፌ ተቀምጦ መዋልን የጠሉ እንደ ረደላ ያሉ ወጣቶች የእግር ጉዞ ማድረግንናከከተማ ራቅ ብሎ ተራሮችን በመውጣት አይምሮአቸውን ለማደስ ይሞክራሉ።
እነዚህ ወጣቶች አዲስ ሀይኪንግ በተሰኘ በፌስቡክ ድህረ-ገፅ አማካኝነት በተከፈተ ማህበረሰብ የተለያዩ ከከተማ ውጪየሚደረጉ ጉዞዎችን በማዘጋጀት በርካቶች የተራራ መውጣት ልምድ እንዲስፋፋ እያደረጉ ይገኛሉ። የዚህ ቡድን መስራችናአስተባባሪ ደግሞ ቢኒያም ሸሪፍ የተሰኘ ወጣት ነው።
ቢኒያም የጂም አሰልጣኝ ነው። በግሉ ያደርገው ከነበረው የእግር ጉዞ ልምድ በመነሳት በቅርቡ ያሉ ጉዋደኞቹናየሚያሰለጥናቸውን ሰዎች በማስተባበር የጀመረው የአዲስ ሀይኪንግ ቡድን ዛሬ ከ17 ሺህ በላይ አባላትን አፍርቷል። ዶክተሮች፣አርክቴክቶች፣ ሰዓሊዎች፣ ደራሲዎች፣ ተማሪዎችና ሌሎች በተለያዩ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ ወጣቶች በዚህ የፌስ ቡክ ገፅአማካኝነት እየተገናኙ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ተራራዎችን ከመውጣት ባለፈ፣ ትልቅ ቤተሰባዊ ትስስርምመመስረታቸውን ቢኒያም ያስረዳል።
ረደላም ረግም የእግር ጉዞንና ተራራ መውጣትን በግሉ የጀመረው ቢሆንም የአዲስ ሀይኪንግ ቡድን መመስረት ግን ልምዱንይበልጥ እንዲወደውና እንዲያዘወትረው እንዳደረገው ይናገራል።
የአዲስ ሀይኪንግ አባላት እስካሁን እንጦጦ፣ ሱባ፣ ሞገሌ፣ ጓሳ፣ አንኮበር ወንጪ አንድ ባሌ ተራራዎች የመሳሰሉ ቦታዎች ተጉዘው ከማያውቋቸው የሀገራቸው ክፍሎች ጋር ተዋውቀዋል፣ ብርቅዬ እንስሳትን ጎብኝተዋል፣ በግላቸው መቼም ያማይረሷቸውን ትዝታዎች አፍርተዋል። ተራራ ከመውጣት ባሻገርም በሚሄዱባቸው ቦታዎች ላይ ለሚኖሩና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የአቅማቸውን ገንዘብ በማሰባሰብ ድጋፍ ያደርጋሉ። ቢኒያም እነዚህ ተግባራት ወጣቶቹን የተራራ መውጣቱን ልምድ ከስፖርትም ባለፈ እንዲያየው እንደሚረዳው ይገልፃል።
በአዲስ ሀይኪንግ ውስጥ በበጎ ፈቃደኛነት የማስተባበር ስራ የሚሰርው ረደላ ቀጣይ ህልሙ ራስ ደጀንና የኪሊማንጃሮን ተራራመውጣት ነው። ከአፍሪካም ተሻግሮ አልፎ የኤቨረስትና ሂማሊያን ተራሮች የመውጣት እድለኛ ከሆነም አንታርቲክ ላይ ኑሮንየመሞከርም ህልም አለው። እሩቅ ይሁን ቅርብ ግን ለረደላና አብዛኞቹ የአዲስ ሀይኪንግ አባላት ህይወት እስካለ፣ ጉዞ ይቀጥላል።