በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ ሴት ተማሪዎች ከወንድ አቻዎቻቸው በበለጠ ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ


ፎቶ ፋይል
ፎቶ ፋይል

በኢትዮጵያ ወደ ትምህርት ቤት የሚገቡ የሴት ህፃናት ቁጥር ከግዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢሄድም አሁንም ሴት ተማሪዎች አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች የሚማሩ በመሆናቸው ከወንድ አቻዎቻቸው በበለጠ ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ። ቀድመው ከነበሩት በሴቶች ትምህርት ዙሪያ ግንዛቤ ማነስ፣ የአቅም ውሱንነት፣ ያለእድሜ ጋብቻና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች በተጨማሪም፣ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በብዛት የሚስተዋለው ህገወጥ ስደት ለሴት ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ ምክንያት መሆኑን የትምህርት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በባህርዳር ከተማ ቀበሌ አንድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ብርቱካን ጀምበሩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ጨርሳ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ስትሻገር ከትምህርቷ ይልቅ የሚያሳስባት የቤተሰቧ አቅም ማነስ እና የፅዳት ስራ እየሰራች የምታሳድጋት እናቷን ማሳረፍ የምትችልበት መንገድ ነበር። በወቅቱ 18 አመት እንኳን ያልሞላት ብርቱካን ወደ አረብ ሀገር ሄዳ እየሰራች ለእናቷ ገንዘብ መላክ እንደምትችል ስትሰማ ለአፍታ አላመነታችም። እናቷ ተበድራ ባመጣችው ገንዘብ በልጅነት እድሜዋ ወደ ሳውዲ አመራች።

ብርቱካን ካሰሪዋ ጋር መስማማት ባለመቻልዋ በአንድ አመት ግዜ ውስጥ ወደ ሀገሯ ስትመለስ ባል በማግባት ኑሮን ለማሸነፍ ሞከረች "ግን እሱም አልተሳካም" ትላለች ብርቱካን።

ልክ እንደ ብርቱካን በአፍላ እድሜያቸው ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው፣ የቤተሰባቸውን የኑሮ ሁኔታ ለመደጎም ወደ አረብ ሀገራት የሚፈልሱ ሴት ህፃናት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱንና፣ ይሄም ትምህርታቸውን ለሚያቋርጡ ሴት ተማሪዎች ምክንያት መሆኑን የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው መምህራንና የትምህርት ቢሮ ሀላፊዎችም ያስረዳሉ።

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ዶክተር ይልቃል ከፍያለ እንደገለፁልን በአሁኑ ሰዓት በክልሉ እንደ ያለ እድሜ ጋብቻ ከመሳሰሉት ባህላዊ ተፅእኖዎች በበለጠ በቤተሰባቸው የኑሮ አቅም ምክንያት የሴቶች ህፃናት ፍልሰት ለትምህርት ማቋረጣቸው ዋነና ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ።

አብዛኞቹ ሴት ህፃናት ትምህርታቸውን አቋርጤው ከሀገራቸው የሚወጡት በህገ-ወጥ መንገድ፣ በደላላ አማካኝነት ነው። ለጉዞ የሚሆን ገንዘብም ስለማይኖራቸው ነገ ልጆቹ ሰርተው ይከፍላሉ በማለት ቤተሰቦቻቸው ንብረታቸውን ሸጠው አሊያም ተበድረው ልጆቹን በብዛት ወደ አረብ ሀገራት ይልኳቸዋል።

በአማራ ክልል 26 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖር የሚያስረዱት አቶ ይልቃል፣ ሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የምትፈታበት አቅም ላይ ባለምድረሷ በአቋራጭ ገንዘብ አግኝቶ ቤተሰብን ለማገዝ የሚደረግ ጥረት ለህገወጥ ፍልሰት ይዳርጋል ይላሉ።

በሀገርቱ ውስጥ እየተባባሰ የሄደው የተመረቁ ተማሪዎች ስራ አጥነትም፣ ሴቶች በትምህርታቸው እንዳይገፉ እንደሚያደርጋቸውም ይገለፃል። በጉዳዩ ላይ ያናገርነውና በባህርዳር ከተማ ኤስ ኦ ኤስ ትምህርት ቤት መምህር የሆነው ደጉ ምናለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው የሴት ተማሪዎች ህገወጥ ፍልሰት ከምጣኔ ሀብት ዝቅተኛ መሆን በተጨማሪ ተምረን የትም አንደርስም ከሚል አስተሳሰብ የመጣ መሆኑን ያስረዳል።

በአሁኑ ሰዓት ከእናቷ ጋር ሆና ሽሩባ በመስራት የምትደዳደረው ብርቱካን በልጅነት የሞከረችው የመጀመሪያው የሳውዲ ጉዞዋ ባይሳካላትም ቤተሰቧ ካለበት የኢኮኖሚ ችግር አንፃር፣ አሁንም ወደ አረብ ሀገር ሄዳ ገንዘብ ማግኘት እመርጣለሁ ትላለች።

ከህገወጥ ፍልሰት በተጨማሪ ታዳጊ ህጻናት በጾታቸው ምክንያት ሲደርስባቸው የኖረው የሀይል ጥቃት፣ እንያለዕድሜ ጋብቻና የመሳሰሉት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተለይ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍሎች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው።

ሰሜን ሸዋ መረሀቤቴ ውስጥ፣ ለሚ ተብላ በምትጠራ መንደር ተወልዳ ያደገችው ሀና ደቹ ገና በለጋ እድሜዋ የአራተና ክፍል ተማሪ እያለች ይህን አይነቱን ያለእድሜ ጋብቻ ለማምለጥ አዲስ አበባ የምትኖር አክስቷን ለምና በመምጣቷ ዛሬ 9ኛ ክፍል ደርሳለች። ለሚ ቀርታ ትማር የነበረችው ታናሽ እህቷ ግን በ 15 አመቷ ከ 8ኛ ክፍል አቋርጣ በቅርቡ ልታገባ ቤተሰቦቿ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ሀና በሀዘን ትናገራለች።

በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በድባቅና ዳንጉር ወረዳዎች ከ25 አመታት በላይ በትምህርት ባለሙያነት ያገለገሉትና በአሁኑ ሰአት በባህርዳር ከተማ አስተዳደር መሸንቲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ሙሉጌታ እድሜውገፍቶ በቤንሻንጉልና በአማራ ክልል ያሉትን ችግሮች አነፃፅረው እንዲህ ያስረዳሉ።

አቶ ሙሉጌታ እንደገለፁልን በቤንሻንጉል ጉምዝ እሳቸው መምህር ሆነው ባገለገሉባቸው አካባቢዎች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተቋማት ከ 15 ወደ 50 ከፍ እንዲሉ ቢደረግም፣ የሁለተኛ ደረጃ ተቋማት ግን ሶስት ብቻ በመሆናቸውና፣ በቅርብ ርቀትም ላይ ስለማይገኙ ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ደንጉር ወረዳ በሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት ለመቀነስና በርቀት ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለመገዝ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ለማቋቋም ጥረት እንደተድረገ አቶ ሙሉጌታ ይገልፃሉ። ነገር ግን ያለው ችግር ህብረተሰቡ ለሴቶች ትምህርት ካለው ግንዛቤ ማነስ ጋር ተደምሮ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መፍታት አልተቻለም።

በአካባቢያቸው የትምህርት ተቋም ባለመኖሩ ከከተማቸው እርቀው ለመኖር የሚገደዱ ሴት ተማሪዎች ከሚደርስባቸው ፆታዊ ትንኮሳ በተጨማሪ በትንሽ ነገር በመታለል ያላሰቡት ኑሮ ውስጥ እንደሚገቡም በባህርዳር ኤስ ኦ ኤስ አስተማሪ የሆነው ደጉ ያስረዳል።

ደጉ ሌላው የሚያሳስበው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፓለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተማሪዎች ላይ የሚደርሲ ችግሮች ናቸው። እነዚህ ችግሮች ወላጆች በተለይ በተለያዩ ክልሎች ያሉ ዩንቨርስቲዎች ውስጥ የሚመደቡ ሴት ልጆቻቸውን ለመላክ እንዲፈሩ እንደሚያደርጋቸው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በዚህም ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ሴት ተማሪዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ደጉ ይገልፃል።

በኦሮሚያ ክልል፣ በነቀምት ከተማ የሴት ተማሪዎችን የትምህርት ተግዳሮት ሁኔታ ለማወቅ ያናገርናቸው የነቀምቴ ከተማ ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አሸናፊ ከበደ ሁንዴሳ በበኩላቸው በከተማው ያለ እድሜ ጋብቻና ሌሎች ባህላዊ ተፅእኖዎች በአንፃራዊነት ዝቅተኛ መሆናቸውንና ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ሴት ተማሪዎች ቁጥር 1.3 ከመቶ ብቻ መሆኑን ነግረውናል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለም ዙሪያ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው በሴት ህፃናት ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶች፣ ያለ እድሜ ጋብቻና የቤት ውስጥ ስራ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች አመልክተዋል። ለወትሮው በሴት ተማሪዎች ዙሪያ የሚደርሱ ችግሮችን በቅርበት የሚከታተሉትና የመረጃ ምንጭ ሆነው የሚያገለግሉት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ግን በአሁኑ ሰዓት ሴት ህፃናት ላይ እየደረሱ ያሉ ተግዳሮቶች ለመከታታል የበለጠ አዳጋች እንደሆነ የትምህርት ባለሙያዎቹ አስረድተዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

በኢትዮጵያ ሴት ተማሪዎች ከወንድ አቻዎቻቸው በበለጠ ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:15:30 0:00


XS
SM
MD
LG