ዘመናዊ የግብርና ዘዴ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን መግታት ረሃብን ለማጥፋት ቁልፍ እንደሆኑ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ምኒስትሩ አዲስ አበባ ለሶስት ቀናት በሚቆየው “ከረሃብ ነጻ ዓለም” በተሰኘ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በዓለም የሚታየውን የምግብ ችግር ለመቅረፍ ፈጠራ የታከለበት መፍትሄ እንደሚያሻም ጠቁመዋል።
“ዘላቂነት ያለው አሰራር፣ የተሻሻለ ዘመናዊ የእርሻ ዘዴ፣ የግርብና ግብአት አቅርቦት ማስፋፋት እና የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን መቅረፍ ለምርታማነት መሻሻል አስፈላጊ ናቸው” ሲሉ ጠቅላይ ምኒስትሩ በ'X' ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መልዕክታቸውን አስፍረዋል።
የዓለም መሪዎች፣ ባለሙያዎች፣ እና ተሟጋቾች ፈጠራ የታከለበት መፍትሄ ላይ ውይይት እንዲያደርጉና በአንድነት እንዲሰሩ በማድረግ ረሃብን ለማጥፋትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት እና ከአፍሪክ ኅብረት ኮሚሽን ጋራ በመተባበር ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ 1ሺሕ 500 የሚሆኑ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ከተባበሩት መንግስታት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም