ዜሌንስኪና ብሊንክን ዩክሬን ውስጥ ተወያዩ

  • ቪኦኤ ዜና

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክ ኪየቩ፣ ዩክሬን 9/8/2022

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ትናንት በድንገት ዩክሬን ከገቡት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ተነገረ፡፡

“ሩሲያን እንደ አሸባሪ አገር” መፈረጅን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች መነጋገራቸውን ዜሌነስኪ በየዕለቱ ምሽት በሚያሰሙት የትናንቱ ንግግራቸው አስታውቀዋል፡፡

ዜሌነስኪ በዚሁ ንግግራቸው “የህግ እውነታው ሁልጊዜም ከተጨባጩ እውነታ ጋር አብሮ መታየት አለበት፡፡ እውነታው ሩሲያ በዓለም ትልቋ የሽብርተኝነት ምንጭ እየሆነች መጥታለች፡፡” ብለዋል፡፡

“የሩሲያ ሽብር በዝምታ የማይታለፍ ስለመሆኑ ዓለም ከወዲሁ በማያሻማ መልኩ ምልክቱ ሊደርሰው ይገባል” ሲሉም አክለዋል ዜሌንስኪ፡፡

ከነሐሴ 26 ጀምሮ ከአንድ ሺ ስኲዌር ኬሎ ሜትሮች በላይ የሚሆነውን የአገራችን ግዛት ነጻ አውጥንተናል በማለት የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ “ይህን ላስቻሉት ሁሉ ምስጋኔዬን አቀርባለሁ፡፡ በእነኚህ ቀናት የዩክሬን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲወለበለብ ያደረገቱን ሠራዊቱን፣ የደህንነት ሠራተኞቻችንን የልዩ ልዩ ኃይሎቻችንን ሁሉ አመሰግናለሁ” ብለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከንም ከዜሌንስኪ ጋር ከተወያዩ በኋላ በሰጡት መግለጫ “በግንባር የሚገኙት አስደናቂዎቹ የዩክሬን ተከላካዮች ለአገራቸው የሚያደርጉትን ፍልሚያ በጀግንነት ይቀጥሉበታል” ብለዋል፡፡

“የፈለገውን ያህል ጊዜም ቢፈጅ” ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምትሰጠውን ድጋፍ ትቀጥላለች በማለት ፕሬዚዳንት ባይደን የገቡትንም ቃል ከፍተኛው የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማት በመግለጫቸው በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬንና “በወደፊቱ የሩሲያ ወረራ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ለተባሉ” ሌሎች 18 አገሮች የ2.2 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ለዩክሬን ደግሞ በቀጥታ 675 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች በእርዳታ እንደምትሰጥ ትናንት ሀሙስ ማስታወቋ ተመልክቷል፡፡