ከኢራን ወደ የመን የተላከ መሣሪያ ተያዘ

  • ቪኦኤ ዜና
ኤ.ኬ.-47 ጠመንጃዎች

ኤ.ኬ.-47 ጠመንጃዎች

ከኢራን ወደ የመን የተላኩ ናቸው የተባሉ ሁለት ሺህ የሚሆኑ ኤ.ኬ.-47 ጠመንጃዎችን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መያዙን የአሜሪካ ባህር ኃይል አስታውቋል።

ከባህር ኃይሉ የወጣው መግለጫ እንዳለው 2,116 ኤ.ኬ.-47 ጠመንጃዎቹ የተያዙት በኦማን ባህረ-ሰላጤ በዓሳ አስጋሪ መርከብ ውስጥ ሲሆን፤ መርከቡ በተለምዶ በኢራን ለሚደገፉት የየመን ሁቲ አማጺያን ሕገ-ወጥ መሣሪያዎች በሚተላላፉበት መሥመር ላይ እንደተያዘ ባህር ኃይሉ ጨምሮ ገልጿል።

የአሜሪካ ኃይሎች ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ሁለት የዓሳ አስጋሪ መርከቦችን መያዛቸውንና መርከቦቹም ከኢራን ወደ የመን የሚተላለፍ መሣሪያ ጭነው እንደነበር መግለጫው አውስቷል።

መርከቦቹ በኢራን ይሚካሄደውን አፍራሽ እንቅስቃሴ የሚያመለከቱ ናቸው ሲሉ በአካባቢው የአሜሪካ ባህር ኃይል አዛዥ ብራድ ኩፐር ተናግረዋል። የአካባቢውን ሰላም የሚያውኩ እንቅስቃሴዎችን በንቃት እንደሚከታተሉም አዛዡ ጨምረው አስታውቀዋል።

ኢራን በተደጋጋሚ ውንጀላውን ብታስተባብልም፣ የተመድ ገለልተኛ አጥኚዎች በመርከብ የሚያዙ መሣሪያዎች ከኢራን የሚመጡ ስለመሆኑ ማስረጃ ይዘዋል።

ሁቲዎች የየመን መዲናን ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ሲቆጣጠሩና በሳዑዲ የሚመራ ጥምር ጦር ከየመን ስደተኛ መንግሥት ጎን በመሆን በግጭቱ ሲሳተፍ አገሪቱ ወደለየለት ትርምስ ውስጥ ገብታለች።

ግጭቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመናውያንን ሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂ አድርጓቸዋል።