የየመን ሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር ላይ በሚመላለሱ መርከቦች ላይ ከፍተኛ የተባለ የድሮን እና የሚሳዬል ጥቃት መፈፀማቸውን ባለሥልጣናት ዛሬ ረቡዕ አስታውቀዋል።
በምላሹ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ የባሕር ኃይሎች የሁቲን ተወንጫፊዎች መትተው ጥለዋል ተብሏል።
አማፂያኑ ጥቃታቸውን የሚሰነዝሩት እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ጦርነት እንድታቆም ለማስገደድ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ጥቃቶቹ ከእስራኤል ጋር ግኑኝነት በሌላቸው መርከቦች ላይም የሚፈጸሙ ሲሆን፣ እስያን እና መካከለኛው ምሥራቅን ከአውሮፓ ጋር የሚያገናኘውን የንግድ መተላለፊያ ማወኩ ተነግሯል።
ለአማፂያኑ ጥቃቶች ምላሽ አሜሪካ በየመን ላይ ጥቃቷን የምትሰነዝር ከሆነ፣ በአገሪቱ ያዝ ለቀቅ የሚያደርገውን የተኩስ አቁም ሊያስተጓጉል ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሯል።
በኢራን ይደግፋሉ የሚባሉት የሁቲ አማፂያን አዲስ ጥቃት የመጣው፣ የተመድ የፀጥታው ም/ቤት ዛሬ ረፋዱ ላይ አማፂያኑ በቀይ ባሕር ላይ በተከታታይ የፈጸሙትን ጥቃት የሚያወግዝ እና እንዲያቆሙም የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው።
በአካባቢው የሚመላለሱ መርከቦች ሚሳዬል እየተተኮሰባቸው፣ ድሮንም ከሰማይ እያንዣበባቸው እንዲሁም በትናንሽ ጀልባዎች ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
በአካባቢው ካለች የአሜሪካ አውሮፕላን ጫኝ መርከብ ላይ የተነሱ ተዋጊ ጄቶች 18 ድሮኖችን፣ ሁለት ክሩዝ ሚሳዬሎችን እና ፀረ መርከብ ሚሳዬሎችን መተው መጣላቸው ተነግሯል።