የዓለም ዋንጫ እግር ኳስ በድምቀት ቀጥሏል

ዛሬ አሥራ አንደኛ ቀኑን የያዘው 19ኛው የዓለም ዋንጫ እግር ኳስ የጨዋታ ውጤቱን ጠብቆ በድምቀት ቀጥሏል።

ትላንት ከተካሄዱት ሦስት ጨዋታዎች መካከል ከሞት ምድብ ውስጥ የብራዚልና የኰት ዲ ቯር ግጥሚያ በጉጉት የተጠበቀውን ያህል በማራኪ ጨዋታ ታጅቦ የመሸናነፍ ፉክክር ታይቶበታል። በውጤቱም የብራዚል ቡድን 3 ለ 1 አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል። ለእረፍት የወጡት በብራዚል 1 ለባዶ ቀዳሚነት ሲሆን፥ ከእረፍት መልስ 2 አክሎ ሙሉ 3 ነጥብ ጨብጧል። ከግብ ክልል ደርሶ ኳስና መረብን የማገናኘት ብቃቱን ያሳየው ሉዊስ ፋቢአኖ፥ ለብራዚል ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ሪካርዶ ካካ ጣጣቸውን የጨረሱ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ለሦስቱም ግቦች መቆጠር ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ሆኖም ወደ መጨረሻው አካባቢ በሁለት ቢጫ ካርድ ቀይ ተሰጥቶት ከሜዳ ተባሯል።

የሜክሲኮ ደጋፊዋች

ለኰት ዲቯር ብቸኛዋን ጐል በግንባሩ ገጭቶ ያስቆጠረው ዝነኛው ዲዲዬ ድሮግባ ነው። ከዚች ግብ ቀደም ብሎም ድሮግባ ተመሳሳይ ሙከራ አድርጐ ኳስ ለጥቂት ወጥታበታለች። አንድ ነጥብ ብቻ ያለው ብሄራዊው የኰት ዲቯር ቡድን፥ አንድ ጨዋታ ከሰሜን ኰሪያ ጋር ስለሚቀረው ትላንት ከብራዚል ጋር ያሳየውን ብቃት ከደገመው፥ አሸንፎ ለማለፍ እድሉ አልተሟጠጠም።

በሌላ ምድብ ፓራጓይ ስሎቫኪያን 2 ለ 1 ስትረታ፥ በኳስ እጅግም የማትታወቀው ኒው ዚላንድ፥ ያለፈውን የዓለም ሻምፒዮና ጣሊያንን ገትራ አምሽታ 1 ለ 1 አቻ ተለያይታለች።

እስካሁን በተደረጉት ጨዋታዎች፥ ከተጠበቁት ይልቅ ያልተጠበቁት ክስተቶች ይበዛሉ። በምድብ ማጣሪያው ላይ አንዳንድ ያልተነገረላቸው ቡድኖች፥ በዝነኞቹ ላይ ያሳዩት በጨዋታ የበላይነትና ያስመዘገቧቸውም ውጤቶች፥ ቅድሚያ ግምቶችን አፋልሰዋል። ክስተቶቹ፥ በእግር ኳስ ትልቅና ትንሽ የሚባልበት ዘመን ላይ አለመሆናችንንም አሳይተዋል። በዓለም ዋንጫ ታሪክ የተካበተ ልምድና ጠንካራ አቋም ያለው የጀርመን ቡድን፥ በኳስ ዝና ትንሽ አገር በሴርቢያ የደረሰበት የአንድ ለባዶ ሽንፈት፥ በቀጣይ ውድድሮች ምን ይፈጠር ይሆን ? አሰኝቷል።

የአፍሪቃው አልጄሪያ ቡድን በታላቋ ብሪታንያ ላይ ያሳየውም የበላይነት በግብ ብልጫ አሸናፊነት አለመታጀቡ የሚያስቆጭ ነበር። በዚህኛውም ጨዋታ የእንግሊዝ ቡድን በአልጄሪያ አለመሸነፉ፥ እድለኛ አሰኝቶታል።

የአፍሪቃ ተስፋ ይሆናሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው የካሜሮኖቹ የማይበገሩ አንበሶች ግን በስም ብቻ ቀርተዋል። በጃፓንና በአውስትራሊያ ቲሞች ተሸንፈው ከጨዋታ ውጭ ሆነዋል።

ዛሬ የ G ምድቦቹ ፖርቱጋልና ሰሜን ኰሪያ ገጥመው ፖርቱጋልች ሰሜን ኰሪያዎቹን ጐል እንደ ቆሎ ሲያቅሙ ታይተዋል። ሰባቱን ነው ያስገቡባቸው።

ሌላው ጨዋታ የ H ምድቦቹ ቺሌና ስዊዘርላንድ ያደረጉት ነበር። ጥሩ ፉክክር ታይቶበትም ነበር። ከ31ኛው ደቂቃ ጀምሮ በ10 ተጫዋቾች ብቻ የተጫወተው ስዊዘርላንድም መጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በገባበት ግብ 1 ለ0 ተሸንፏል።

ስፔንና ሆንዱራስ የቀኑን የመጨረሻ ጨዋታ ይጫወታሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ የፈረንሳይ ቡድን በውጤትና በውስጣዊ የዲሲፕሊን ድርቅ ተመትቶ፥ በጊዜ ወደ አገሩ ለመመለስ ተቃርቧል።