"26 ድሃ ሀገራት እአአ ከ2006 ወዲህ ባልታየ ደረጃ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል” የዓለም ባንክ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፡ የዓለም ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ዋሽንግተን፣ ዲሲ

ከዓለም እጅግ ድሃ ህዝብ አእርባ ከመቶው የሚኖርባቸው 26 ድሃ ሀገራት እአአ ከ2006 ወዲህ ከምንጊዜውም በከፋ ከፍተኛ እዳ ውስጥ እየተዘፈቁ፣ ለተፈጥሮ አደጋዎች እና ሌሎች ቀውሶች እየተጋለጡ መሆኑን የዓለም ባንክ ጥናታዊ ዘገባ አመለከተ፡፡

ትላንት የወጣው ጥናታዊ ዘገባው እንዳመለከተው ምንም እንኳ የተቀረው የዓለም ክፍል ከኮቪድ 19 ቀውስ በማገገም ጉዞውን የቀጠለ ቢሆንም፣ እነዚህ ኢኮኖሚዎች ግን ወረርሽኙ ዋዜማ ከነበሩት አንጻር ሲታዩ ዛሬ በአማካይ የበለጠ የደኸዩ ሆነዋል፡፡

በዋሽንግተን ከሚካሄዱት የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት አመታዊ ስብሰባዎች በአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የተለቀቀው ጥናታዊ ዘገባው የከፋ ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ትልቅ ችግር መኖሩን ያረጋገጠ ነው ተብሏል፡፡

እነዚህ ሀገራት በዓለም አቀፍ ልማት ማህበር (አይ ዲ ኤ) እርዳታ እና ብድር ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጥገኛ በመሆናቸው ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ላይ ያለውን ውድቀትም ያሳየ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የዓለም ባንክ በዚህ አመት በአለም እጅግ ድሃ ለሆኑት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ 100 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ የሚያደርገውን ጥረት አጉልቶ እንደሚያሳይም ተመልክቷል፡፡

የሀገራቱ ዕዳ ከአጠቃላይ ምርት ገቢያቸው (GDP) አንጻር ሲሰላ 72 በመቶ መደረሱም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ ይህም በ18 ዓመታት ውስጥ ሲታይ ከፍተኛው ሲሆን ከእነዚህ ሀገሮች ውስጥ ግማሾቹ በእዳ ማጥ ውስጥ የተዘፈቁ ወይም ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጡ ናቸው ተብሏል።

ከእነዚህ ሀገራት መካከል ሁለት ሶስተኛዎቹ በትጥቅ ግጭት ውስጥ የሚገኙ ወይም ፀጥታን የማስከበር ፈተናዎች ገጥሟቸዋል፣ ይህ ደግሞ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ የሚያበረታታ ባለመሆኑ በርካቶች ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ ብቻ እንዲተማመኑ በመገደዳቸው ለኢኮኖሚ አለመረጋጋት ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው ተዘግቧል፡፡

የተፈጥሮ አደጋዎች በነዚህ ሀገራት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳደሩ ሲሆን እኤአ በ2011 እና 2023 ባለው ጊዜ አመታዊ ኪሳራቸው በአማካይ በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት የሁለት ከመቶ ኪሳራ ያሳደረባቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የዓለም ባንክ ዋና ኢኮኖሚስት ላለፉት አምስት አመታት በተለይም ሌሎች የፋይናንስ ምንጮች እየቀነሱ በመጡበት ወቅት ዓለም አቀፍ ልማት ማህበር (አይዲኤ) ለሀገሮች ወሳኝ የሆነ የፋይናንስ ምንጭ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ዓለም አቀፉ የልማት ማሕበር በየሦስት ዓመቱ ከዓለም ባንክ አባል ሐገሮች መዋጮ ገንዘብ የሚያገኝ ሲሆን እኤአ በ2021 ከፍተኛው የሆነው የ93 ቢሊዮን ዶላር መዋጮ ሰብስቧል፡፡ የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ኤጄይ ባንጋ እ አ አ እስከ ታሕሳስ 6 ባለው ጊዜ ቃል የተገባውን 100 ቢሊዮን ዶላር እና ከዚያም በላይ ለመሰብሰብ አቅደዋል፡፡

እነዚህ ሀገራት የግብር አሰባሰብ ስርዓቶችን በማሻሻል ፣ መንግስታዊ ወጪን የበለጠ ውጤታማ በማድረግ የውጭ ዕርዳታ ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ ፣ የራሳቸውን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸው ሪፖርቱ አመልክቷል።