የሳህል ክልል አገሮች የጸጥታ ችግራቸውን እንዲፈቱ ዓለም ባንክ አሳሰበ

  • ቪኦኤ ዜና
የዓለም ባንክ ፕሬዚንት ዴቪድ ማልፓስ

የዓለም ባንክ ፕሬዚንት ዴቪድ ማልፓስ

የአፍሪካ የሳህል ክልል በልማት ለመበልጸግ "የደህንነት ፈተናዎቹን ማሸነፍ አለበት" ሲሉ በክልሉ የሁለት ቀናት ጉብኝታቸውን ያጠናቀቁት የዓለም ባንክ ፕሬዚንት ዴቪድ ማልፓስ አሳሰቡ፡፡

የሳህል አካባቢ ለዓመታት በጂሃዲስቶች ሁከት የተወረሰ ሲሆን ማሊ 11 ዓመታት የዘለቀውን ሁከት ለማስቆም ስትታገል ቆይታለች፡፡ በአካባቢው ያለው አለመረጋጋት ምክኒያት በመቶ ሺሆች የተቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። ሌሎች ብዙ መቶ ሺዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡

በከባድ ሁከት ከሚታመሱ ድሃ አገሮች አንዷ ሌላይቱ የክልሉ ሀገር ቡርኪና ፋሶም በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር በ2022 ሁለት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች ተፈጽመውባታል፡፡

እነዚህን ችግሮች የጠቀሱት የዓለም ባንኩ ፕሬዚዳንት “ደህንነት ለልማት ወሳኝ መሆኑን እንገንዘባለን፡፡ በሳህል ውስጥ ያለው የደህንነት ሁኔታ ከባድ ፈተና ነው” ብለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን በአፍሪካ ጉብኝት ከአካሄዱ ከሁለት ሳምንታት በኋላ አህጉሪቱን የጎበኙት ዴቪድ ማልፓስ “የዓለም ባንክ ለኒጀር፣ ለሳህል እና በአጠቃላይ ለአፍሪካ ድጋፍ እንደሚሰጥ ሳረጋግጥ በደስታ ነው” ሲሉ በጉብኝታቸው ማጠናቀቂያ ላይ መናገራቸውን የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡