በአሁኑ ወቅት ከሰሃራ በታች ያለው የአፍሪካ አካባቢ አዲሱ የሁከት ተጠቃሚ እስላማዊ ጽንፈኝነት መፈልፈያ ሆኗል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው አዲስ ሪፖርት አስታወቀ።
የመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም አቀፍ ልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ዛሬ ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርቱ በአካባቢው ሰዎች ጽንፈኛ እስላማዊነትን የሚቀላቀሉት በአመዛኙ ከሃይማኖታዊ ይበልጥ በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች እንደሆነ ሪፖርቱ አመልክቷል።
የመንግሥታቱ ድርጅት አዲስ ሪፖርት እንዳለው እአአ በ2017 በወጣው የቀደመው ሪፖርት ላይ ከሚታዩት አሃዞች ጋር ሲነጻጸር 92 ከመቶው ተመልማዮች ጽንፈኛ ቡድኖችን የተቀላቀሉት ባሉበት የከፋ ድህነት ምክንያት የተሻለ መተዳደሪያ ለማግኘት ብለው ነው።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፥ የዋጋ መናር እና የአየር ንብረት ለውጥ በበርካታ አፍሪካውያን የኑሮ መተዳደሪያ ላይ ከባድ ጫና ማሳደሩን ሪፖርቱ አውስቷል።
አያይዞም ሃይማኖታዊ በሆኑ ምክንያቶች ጽንፈኛ ቡድኖችን የሚቀላቀሉ ሰዎች ቁጥር በ57 ከመቶ መቀነሱን ሪፖርቱ ጠቁሟል።
የተመዱ የዓለም አቀፍ ልማት ፕሮግራም ለዚህ ሪፖርቱ ሶማሊያ፥ ሱዳን፥ ናይጄሪይ፥ ማሊ፥ ቻድ፥ኒጀር ፥ ቡርኪና ፋሶ እና ካሜሩን ውስጥ ቁጥራቸው ወደ2200 የሚጠጋ ሰዎችን አነጋግሯል።
ከመካከላቸው ከ1100 የሚበልጡት በፍላጎት ወይም ተገድደው ኃይል ተጠቃሚ ጽንፈኛ ቡድኖችን የተቀላቀሉ የቀድሞ አባላት መሆናቸው ተጠቁሟል።