ወልዲያ ላይ ተፈፅመዋል በተባሉ ጥቃቶች ጉዳት ደርሷል

ወልድያ

በወልዲያና አካባቢው በተስፋፋው ወታደራዊ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቀው እየወጡ መሆናቸው ተሰምቷል።

በአካባቢው የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ ስለደረሰው ጉዳት፣ ጦርነቱ የሚገኝበት ሁኔታና ሌሎች መረጃዎችን ማግኘት ባይቻልም “የዐይን እማኝ ነን” የሚሉ የውጫሌ ከተማ ነዋሪዎች ወልዲያን ጨምሮ ከስሪንቃና መርሳ አካባቢዎች ሰዎች ሸሽተው ወደ አጎራባቾቻው ውርጌሳ፣ ውጫሌ፣ እንዲሁም ወደ ኃይቅና ደሴ ከተሞች እየገቡ መሆናቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የወልዲያ ከተማ መንግሥታዊ አደረጃጀትም ሆነ ነዋሪዎቹ ከቀናት በፊት “ከተማዋን ከህወሐት ጥቃት ለመታደግ የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ መሆናቸውን” በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተው ነበር፡፡

የወልዲያ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ፅህፈት ቤት በማኅበራዊ ገፁ ባስነበበውና “አስቸኳይ” ሲል በገለፀው መልዕክት ትናንት ለዛሬ አጥቢየ ምሽት ከህወሐት በኩል ከባድ መሳሪያ በተደጋጋሚ መተኮሱን አስታውቋል።

ለመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ተሌቪዥን መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙለነህ “ወረራ ተፈጽሞባቸዋል” በተባሉ አካባቢዎች “በተወሰደ ወታደራዊ ዘመቻ የህወሐት ቡድን እየተደመሰሰ ነው” ብለዋል። ዳይሬክተሩ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል “ህወሐት ተስፋ ቆርጦ በወልዲያ ንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ሠንዝሯል” ብለው ህይወት እንደጠፋበት የጠቆሙት ጥቃት የመንግሥትንና የህዝብ ተቋማትንም ጭምር ዒላማ ያደረገ እንደነበር ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የህወሐት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ታጣቂዎቻቸው ወደ አፋርና ወደ አማራ ክልሎች ዘልቀው መግባታቸውን አምነዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ የልዑካን ቡድን በጋይንት ጨጨሆ አቅጣጫ በመቄት ወረዳ ደብረ ዘቢጥ አካባቢ “የህወሐትን ወረራ ለመመከት ተሰልፏል” የተባለውን የመከላከያ ኃይል፣ የልዩ ኃይል፣ የሚሊሽያና የፋኖ አደረጃጀት እንቅስቃሴ መጎብኘቱ ተገልጿል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

Your browser doesn’t support HTML5

ወልዲያ ላይ ተፈፅመዋል በተባሉ ጥቃቶች ጉዳት ደርሷል