የጤና ድርጅቱ ለአል ሺፋ ሆስፒታል የሕክምና መሣሪያዎች አበረከተ

ፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች በጋዛ አል ሺፋ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ

በጋዛ በሚገኘው የአል ሺፋ ሆስፒታል የደረሰውን ከባድ ውድመት የሚያሳይ ምስል በዓለም ጤና ድርጅት ተለቋል።

20 የቀዶ ጥገና ክፍሎች የነበሩት ሆስፒታል፣ አሁን ፍርስራሽ የተከመረበት ሲሆን፣ በሆስፒታሉ ቅጥር ውስጥም ሰዎች በመገደል ላይ ናቸው የሚሉ ሪፖርቶች በተደጋጋሚ በመሰማት ላይ ናቸው።

የጤና ድርጅቱ የሕክምና ቁሶችን ወደ ስፍራው በመውሰድ አስቸኳይ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በመሞከር ላይ ቢሆንም፣ ካለ ነዳጅ አቅርቦት፣ የሕክምና መሣሪያዎች እና ሠራተኞች መኖር ትርጉም እንደማይኖረው አስተባባሪው ሻን ኬሲ ለአሶስዬትድ ፕረስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

ቁስለኞችን በማከም እና የተጎጂዎችን ውጋት ለመቀነስ በመሞከር ላይ መሆናቸውን የጠቅሱት አስተባባሪው፣ “አንድ ሁስፒታል በጥቃት ላይ እያለ እና ካለ ነዳጅ እንዴት መሥራት ይችላል?” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከፍተኛ አደጋን ሊያስከትልበት የሚችል እንደነበር በገለፀውና ድርጅቱ ባከናወነው ሥራ፣ ለቀዶ ጥገና እና ቁስለኞችን ለማከም የሚያገለግሉ በርካታ መሣሪያዎች፣ ለማዋለድ የሚረዱ ቁሶች እና መድሃኒቶችን ወደ ሆስፒታሉ ማስገባቱን አስታውቋል።

በእስራኤል ጥቃት እስከ አሁን 20ሺሕ የሚጠጉ ፍልሥጤማውያን ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 1.9 ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው እንዲሸሹ አድርጓል።