ረሃብ ወደ ቀቢፀ ተስፋ ድርጊቶች እየገፋ ነው

  • ቪኦኤ ዜና
ፎቶ ፋይል፦ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መጠለያ ካምፕ ውስጥ ለተፈናቀሉ ዜጎች የእርዳታ እህል ሲሰጥ፣ እአአ ጥር 22/2022

ፎቶ ፋይል፦ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መጠለያ ካምፕ ውስጥ ለተፈናቀሉ ዜጎች የእርዳታ እህል ሲሰጥ፣ እአአ ጥር 22/2022

በአፍሪካ ቀንድ ያለው የረሃብ ሁኔታ እየተባባሰ ሲሆን ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አካባቢውን ወደ ጠኔ ምድር እየቀየረው መሆኑ እየተነገረ ነው።

ይህም በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የህይወትና የጤና መከራ መደቀኑና ረሃቡ የጠናባቸው አካባቢዎች ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በህይወት ለመቆይት ሲሉ የቀቢፀ ተስፋ ድርጊቶችን ለመፈጸም እየተገደዱ መሆናቸው ተገልጿል።

ከ37 እስከ 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውንና ራሳቸውን ለመመገብ ሲሉ ንብረታቸውን የሚሸጡበት፣ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ላይ የሚገኙበት እንዲሁም የተለየ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ደረጃ ላይ መሆናቸውን የሚያሳየውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ የተሠራ ትንተናን ጠቅሶ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

የበረታ የገንዘብ እጥረት ስላለባቸው ድርጅቱም ሆነ ሌሎች የረድዔት ተቋማት ረሃቡን ለመቋቋም የሚያስፈልገውን ዕርዳታ ለማድረስ መቸገራቸውን የጤና ድርጅቱ ኃላፊዎች ተናግረዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ህይወትን ለመታደግ የሚያስችል እርዳታ በመጭዎቹ አምስት ወራት ውስጥ በተከታታይ ለማድረስ 124 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው የድርጅቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።