በኡጋንዳ የኢቦላ ወረርሽኝ እንዳከተመ ተገለፀ

ካምፓላ፣ ኡጋንዳ፣ እአአ 3/16/2022

የዓለም ጤና ድርጅት በኡጋንዳ የነበረው የኢቦላ ወረርሽኝ እንዳበቃ ዛሬ አስታውቋል። በጤና ድርጅቱ መመሪያ መሠረት ለ42 ቀናት አዲስ የተያዘ ሰው ከሌለ ወረርሽኙ እንዳበቃ ይቆጠራል።

ባለፈው መስከረም ወረርሽኙ መከሰቱ ከታወቀ በኋላ በኡጋንዳ 142 ሰዎች በኢቦላ ሲያዙ 52 ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

“በኡጋንዳ የኢቦላ ወረርሽኝን በተሳካ ሁኔታ ተቆጣጠርናል” ብለዋል የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ጄን ሩት አሰንግ። የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምም ይህንኑ አረጋግጠዋል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል።

አፍሪካዊቷ አገር ሥርጭቱን ለማስቆም “ጠንካራና ሁሉን አቀፍ ምላሽ” ሰጥታለች ብለዋል ዶ/ር ቴድሮስ፡፡

‘የሱዳን ኢቦላ’ የተባለውና በኡጋንዳ የታየው የኢቦላ ዓይነት፣ በኮንጎ ባለፉት ዓመታት እንደታየውና ‘የዛየር ኢቦላ’ ተብሎ እንደሚታወቀው የኢቦላ ዓይነት ክትባት የለውም። ለተውሳኩ የሚሆን ክትባት ለማግኘት በቅርብ ቀናት ውስጥ ሙከራ ይጀመራል መባሉን የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

ቡኡጋንዳ የተከሰተው ወረርሽኝ በአሜሪካና አውሮፓ የተበረከቱ ክትባቶችን ለመሞከር አጋጣሚ ይፈጥራል ሲል የኤ.ፒ. ሪፖርት ጨምሮ ገልጿል።

ወረርሽኙ የመግደል ዕድሉ 40 በመቶ እንደነበርም የዓለም ጤና ድርጅት ጠቁሟል።