የዓለም የጤና ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ በ30 አመታት ጊዜ ባልታየ መልኩ የከፋ ድርቅ እንደተከሰተ ገልጿል። ህጻናትን አድኑ የተባለው የህጻናት መርጃ ድርጅት በበኩሉ በ50 አመታት ጊዜ ውስጥ ያልታየና የከፋ ብሎታል።
ዶ/ር ሚሸል ጌር (Dr. Michelle Gayer) በዓለም የጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ መከላከልና የሰብአዊ አርዳታ ምላሽ ክፍል ስራ አስኪያጅ ናቸው።
“በኢትዮጵያ የድርቅ ቀውስ የተከሰተው በኤል ኒኖ ምክንያት ነው። ይህ የአየር ለውጥ በበዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ድርቅ ሲያስከትል በሌሎች አከባቢዎች ደግሞ የጎርፍ መጥለቅለቅ ችግር ያደርሳል። በዚህ ምክንያትም ከፍተኛ የምግብ እጥረት ተፈጥሯል። ሰዎች ከአከባብያቸው እንዲፈናቀሉም አድርጓል”ብለዋል።
ይህ ሁኔታም ሰዎች ለተላላፊ በሽታዎችና ለምርቀዛ እንዲጋለጡ ያደርጋል። በተለይም ልጆች በበለጠ ሊጎዱ እንደሚችሉ ዶ/ር ሚሸል ጌር ጠቁመዋል።
“ለምሳሌ ልጆች በቂና የተመጣጠነ ምግብ ካላገኙ ለበሽታ ይጋለጣሉ። ኒሞንያ ማለት የብርድ በሻታ፣ ተቅማጥና ወባ ሊይዛቸው ይችላል። መታመም ብቻ ሳይሆን ሊጠናባቸውም ይችላል። ስለሆነም ፈጣን ህክምና ካልገኙ ሊሞቱ ይችላሉ።”
የአለም የጤና ድርጅት በመጪው ጥር ወር በሚጀመረው የአውሮፓውያን 2016 አም ውስጥ 400,000 የሚሆኑ ልጆች ከባድ የምግብ እጥረት ሊገጥማቸው ይችላል። ሌሎች አንድ ሚልዮን የሚሆኑ ልጆችና ነፈሰ-ጡር ወይም የሚያጠቡ እናቶች ደግሞ መጠነኛ የምግብ እጥረት ይገጥማቸዋል ተብሎ ይገመታል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የገቡ በሽታዎች እንዳሉ ዶ/ር ሚሸል ጌር ያስረዳሉ።
“ገቡ ከተባሉት በሽታዎች መካከል ኩፍኝና ቀጭን ተቅማጥ ይገኙባቸዋል። በሽታዎቹም ንጽህና በጎደለው ውሀና በአጠቃላይ ንጽህና ጉድለት ምክንያት የተከሰቱ ናቸው። ማጅራት ገትር በሽታም ገብቷል። ደንጊ ፊቨር (Dengi fever) የተባለው ትኩሳት የሚለቅ በሽስታ እና እከከ መስል በሽታዎችም አሉ።”
የአለም የጤን ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ቡድን የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን እየረዳ መሆኑን ዶ/ር ሚሸል ጌር ገልጸዋል።
“የጤን ሚኒስቴሩ ስራውን በማቀላጠፍ ረገድ ለመርዳት እንችል እንደሆነ ለማየት እዛው የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ቡድን መድበናል። ከጤናው ሚኒስቴርና ከጤና አጋሮች ጋር ሆነን የጤና አገልግሎት ለማቅረብ እንችል እንደሆነ ለማረጋገጥ እንፈልጋለን። ልጆች ሲታመሙና ህክምና ሲያስፈልጋቸው የህክምና አገልግሎት ለማቅረብ መቻል ማለት ነው” ብለዋል።
የአለም የጤና ድርጅት አስቸኳይ ረድኤት የሚያስፈልጋቸውን ክፍሎች በአንደኛ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ያስቀምጣል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛውን ደረጃ ይዛለች። ኢራቅና ሶርያ ደግሞ ሶስተኛ ናቸው።
የአለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ እአአ ከ 1982 እስከ 84 አም በነበረው ጊዜ ገብቶ የነበረው ረሀብ አስከፊ ሲሆን፣ በጦርነትና ኤል ኒኖ በተባለው የአየር ለውጥ ምክንያት እንደሆነ ይነጋራል። በዛን ወቅት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አልቀዋል። በሚልዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ ተሳቃይተዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን ያ አስከፊ ሁኔታ እንዳይደገም ሲባል ብዙ ነግር ተሰርቷል። ከአስቀድሞ ማስጠንቀቅ አንስቶ ስለ አየሩ ሁኔታ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር እስከማድረግ ድረስ ይሄዳል። የእንግሊዘኛው ክፍል ባልደረባችን ጆ ዲካፑአ ያጠናቀረውን ዘገባ አዳነች ፍሰሀየ አቅርባዋለች ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5