የዓለም የጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ክትባት ማጠናከሪያ በአስቸኳይ በስፋት እንዲዳረስ አጥብቆ ይደግፋል ሲሉ በድርጅቱ አሰባሳቢነት ጉባዔ የተቀመጡ ጠቢባን ተናገሩ። ይህ ከአሁን ቀደም የዓለሙ የጤና ድርጅት ማጠናከሪያ ተጨማሪ ክትባት አላስፈላጊ ነው፣ እንዲያውም ክትባቱ በፍትሃዊነት እንዳይዳረስ ያደርጋል በማለት ሲያሰማ የነበረውን ውትወታ ቀልብሶታል።
የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው መግለጫ በፍጥነት ተላላፊ የሆነው ኦሚክሮን የተባለው የቫይረሱ ዝርያ በዓለም ዙሪያ እየተዛመተ ባለበት በአሁኑ ወቅት ክትባቱ በበሽታው ምክንያት በከፋ ሁኔታ መታመምን እና ሞትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚከላከል የኤክስፐርቶቹ ቡድን ከድምዳሜ የደረሰበት መሆኑን አመልክቷል።
ባለፈው የአውሮፓ 2021 ዓመተ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ክትባቱን ለወሰዱ ሰዎች ማጠናከሪያውን መከተብ እንዲቆም ይልቁንም ባለጸጎቹ ሃገሮች ያላቸውን ክትባት እንዲለግሱ ሲማጸኑ እንደነበር ይታወሳል።