የኮሌራ ወረርሽኝ በበርካታ ሃገራት መስፋፋቱ ተነገረ

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት

ከጥር ወር 2016 ዓ/ም ጀምሮ እስካለፈው ሐምሌ ወር ድረስ ባሉት ጊዜያት በ26 ሃገራት የሚገኙ ከ300 ሺሕ በላይ ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ መጠቃታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በወረርሽኙ በከፍተኛ ደረጃ ከተጠቁት ውስጥ ድርጅቱ ምሥራቃዊ የሜዲትሬኒያን ክልል ብሎ በሚጠራው አካባቢ ወረርሽኙ በከፍተኛ ደረጃ የታየ ሲሆን ቀጥሎ ወረርሽኙ በብዛት የተስተዋለበት ደግሞ የአፍሪካ ክልል ነው።

በአፍ የሚሰጠው የኮሌራ ክትባት በከፍተኛ ደረጃ እጥረት መከሰቱ፣ ለወረርሽኙ የሚሰጠውን ምላሽ ደካማ እንዳደረገ የጤና ድርጅቱ አስታውቋል። በአሁኑ ወቅት 18 ሃገራት 105 ሚሊዮን ክትባቶች እንደሚያስፈልጓቸው ጥያቄ ማቅረባቸውም ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሱዳን የሚካሄደው ጦርነት አንደኮሌራ ያሉ ተላላፊ በሽታዎችን እንዳባባሰ የጤና ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ ኮሌራ የ316 ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈና ከ11 ሺሕ በላይ ሰዎችም በወረርሽኙ እንደተጠቁ የድርጅቱ ባለሥልናት አስታውቀዋል።