የዓለም የጤና ድርጅት ደቡባዊ አፍሪካ ውስጥ የፖሊዮ ሥርጭት መቀስቀሱ ያሳሰበው መሆኑን ገለጸ

ፎቶ ፋይል፦ህፃኑ የፖሊዬ ክትባት ሲሰጠው፣ በሞዛምቢክ አጎራባች አካባቢ ሊሎንግዌ፣ ማላዊ እአአ መጋቢት 20/2022

ሞዛምቢክ በፖሊዮ የተያዘ ሰው መገኘቱን ማረጋገጧን ተከትሎ ማላዊ ዛምቢያ ታንዛንያ እና ዚምባቡዌ ውስጥ የተጠናከረ ቅኝት እንዲካሄድ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡

ሞዛምቢክ ቲቴ በተባለ ክፍለ ግዛቷ አንድ ልጅ በበሽታው መያዙን አረጋግጣለች፡፡ ቀደም ብሎም ማላዊ ባለፈው የካቲት በበሽታው የተያዘ ሰው መገኘቱን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ማትሺዲሶ ሞኤቲ በአምስቱ ሀገሮች ቅኝት እንደሚካሄድ እና በቀጣዮቹ ሳምንታት ውስጥ ለሃያ ሦስት ሚሊዮን ልጆች ክትባት ለማዳረስ እቅድ መያዙን ገልጠዋል፡፡

ዶ/ር ኢንዱታቤ ሞጂሮም በአፍሪካ የዓለም የጤና ድርጅት የፖሊዮ ፕሮግራም አስተባባሪ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው እርምጃ ጥራት ያለው የክትባት መርሃ ግብር ማካሄድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

“ሁለተኛው እርምጃ ደግሞ በሁሉም ሀገሮች የቅኝት ስራ ማከናወን ይሆናል፡፡ ይህ ሲሆን በክልላችን የሚዘዋወረውን የፖሊዮ ቫይረስ በጠቅላላ በጣም በፍጥነት ለመያዝ ይቻላል፡፡ የቅኝት ስራችንን ለሊሎችም ሀገሮች ማዳረስ አለብን፡፡” ብለዋል።

የዚምባቡዌ ለሰብአዊ መብቶች የቆሙ ዶክተሮች ማህበር ሌሎች በሽታዎች የመቀስቀስ እድል ያገኙት ዓለም የኮቪድ-19ን ወረርሺኝን ሲዋጋ የእንቅስቃሴ ገደቦች ሥራ ላይ ከመዋላቸው የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም ብለዋል፡፡

ዚምባቡዌ ከሞዛምቢክ ጋር በሚያዋስናት ድንበር አካባቢ የኩፍኝ ሥርጭት መቀስቀሱን ባለፈው ሳምንት አስታውቃለች፡፡