ሁለት የረድኤት ድርጅቶች በአፋርና ትግራይ ልገሳ ቀጥለናል አሉ

  • ቪኦኤ ዜና
ፎቶ ፋይል - የዓለም የምግብ ፕሮግራም የእርዳታ ድጋፎች ጭኖ በማይ ፀብሪ ከተማ፣ እአአ ሰኔ 26/2021

ፎቶ ፋይል - የዓለም የምግብ ፕሮግራም የእርዳታ ድጋፎች ጭኖ በማይ ፀብሪ ከተማ፣ እአአ ሰኔ 26/2021

ሁለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የረድኤት ወኪሎች በአፋርና በትግራይ የሚያደርጉትን እርዳታ መቀጠላቸውን ዛሬ አስታውቀዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በአፋር እየረዳ መሆኑን ሲያስታውቅ፣ የዓለም አቀፉ የሥደተኞች ድርጅት በበኩሉ በትግራይ ነፍስ-አድን እርዳታ በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግሯል።

ከድርጅቱ የኢትዮጵያ ኃላፊ የቪዲዮ መልዕክት ጋር በትዊተር መግለጫውን ያስተላለፈው የመንግሥታቱ ድርጅት የምግብ ፕሮግራም፣ በአፋር ክልል “እጅግ ለችግር የተጋለጡ” ያላቸውን ኢትዮጵያውያን በመርዳት ላይ መሆኑን አስታውቆ፣ 650 ሺህ ለሚሆኑት አጠቃላይ እርዳታ፣ 110 ሺህ ለሚሆኑት የተመጣጣኝ ምግብ እንዲሁም 96 ሺህ ለሚሆኑ ሕጻናት ደግሞ በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እያደረገ መሆኑን በዝርዝር አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የድርጅቱ ኃላፊ የሆኑት ክላውድ ጂቢዳር በቪዲዮ መልዕክታቸው እንዳሉት፣ ማኅበረሰቡ ከትልቅ ችግር ጋር መጋፈጡንና በተለይ እጅግ ሞቃት በሆነው አፋር የውሃ ችግር ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።

“መንግሥትም ሆነ አጋር ወገኖች ዋናው ማድረግ ያለባቸው ከማኅበርሰቡ ጋር ተቀራርቦ መነጋገር ነው” ሲሉ ተደምጠዋል ኃላፊው።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሥደተኞች ድርጅት በበኩሉ፣ በትግራይ የሚያደርገውን የሕይወት አድን ፕሮግራም እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ አስፈላጊ እርዳታዎችን ሽረ ውስጥ በሚገኙ ስድስት ጣቢያዎች መቀጠሉን አስታውቋል።

ድርጅቱ በትዊተር ባወጣው መግለጫ እንዳለው በሰሜን ኢትዮጵያ የሚያደርገውን እርዳታ በመቀጠል ፕሮግራሙን ከፍ ለማድረግና ለማስፋፋት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል።

በሰሜን ኢትዮያ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት በአፋር፣ አማራና ትግራይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የምግብ ተመጽዋች አድርጓል። በርካቶችም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።