በጋዛ የሚካሄደው ጦርነት ጥላ ያጠላባትና የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ሥፍራ እንደሆነች የምትታመነው ቤተልሄም፣ የነገውን የፈረንጆች ገና ለመቀበል የምትዘጋጀው እንደተለመደው በድምቀት ሳይሆን በሃዘን ድባብ ነው።
ለወትሮው ከመላው ዓለም የሚመጡ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለገና ታስተናግድ የነበረችው ጥንታዊቷ ቤተልሄም፣ ዘንድሮ ምንም ጎብኚ ያልመጣባት፣ በዋናው አደባባይ የገና ዛፍ ያልቆመባት ከተማ ሆናለች፡፡ ቀኑን በሰልፍ ያደምቁ የነበሩት ወጣቶች እና የመብራት ጌጣጌጥ ዛሬ የሉም።
“ሁልጊዜም የቤተልሄም መልዕክት ሰላም እና ተስፋ ነው። በዚህ ወቅትም ይህንኑ መልዕክት ለዓለም እናስተላልፋለን” ብለዋል በእስራኤል በተያዘችው ዌስት ባንክ የምትገኘው የቤተልሄም ከንቲባ አንተን ሳልማን።
“ዓለም የፍልስጤማውያንን ሥቃይና መሬታችን በእስራኤል መያዙን ለማስቆም እንዲሠራ እንጠይቃለን። መብታችን፣ ነፃነታችን፣ ማንነታችን እንዲመለስልንና በእስራኤል መያዛችን በመቀጠሉ ምክንያት ከሚገጥመን አደጋ እንድንጠበቅ ዓለም ይተባበረን” ሲሉም አክለዋል።
በጋዛ ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ በእስራኤልና በእስራኤል በተያዘችው ዌስት ባንክ የጎብኚዎች ቁጥር እጅግ ቀንሷል።
150 ሺሕ ከሚጠጉ ፍልስጤማውያን ውስጥ አብዛኞቹ ለሥራ ወደ እስራኤል እንዳይገቡ በመከልከላቸውም የፍልስጤማውያኑ ኢኮኖሚ ባለፈው አንድ ዓመት 25 በመቶ ቀንሷል።