ሻምቡ ውስጥ የሁለት የትግራይ ተማሪዎች ሕይወት ጠፋ

ወለጋ ዩኒቨርሲቲ

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሻምቡ ግቢ ውስጥ ትናንት በተማሪዎች መካከል በተነሣ ግጭትና ሁከት ሁለት የትግራይ ተማሪዎች መገደላቸው ተገልጿል።

የትግራይና የኦሮምያ ክልሎች የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮዎች ኃላፊዎች በየፌስቡክ ገፆቻቸው ላይ ዛሬ ባወጧቸው መልዕክቶች በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሻምቡ ግቢ ውስጥ ሌሊቱን በተፈጠረ ሁከት የግቢው ተማሪዎች የነበሩ ሁለት የትግራይ ተወላጆች ሌሊቱን ሕይወታቸው ማለፉን አስታውቀዋል።

የትግራይና የኦሮምያ ክልሎች የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮዎች ኃላፊዎች

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ማዕከል የሆነችው ሻምቡ ከተማ አንድ ነዋሪና ሌላ በግቢው የዩኒቨርሲቲው ባልደረባ የሆኑ ባለሙያ ለዝግጅት ክፍላችን ስለ ሁኔታው ሲገልፁ ግጭቱ የተከሰተው አዲግራት ውስጥ ተገድሏል በተባለ ሌላ ተማሪ አጋጣሚ ምክንያት የተነሣሣ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምንም እንኳ ከትምህርት ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ ሰሞኑንም ውጥረት የነበረ ቢሆንም እንዲህ አንድ ጎሣ ላይ ነጥሎ ያነጣጠረ ችግር ግን እንዳልነበረ ቪኦኤ ያነጋገራቸው እማኞች ተናግረዋል።

የሻምቡ ግቢ የትምህርት ጉዳዮች ምክትል ዲን አቶ ቱሊ አብዲሣ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል የመውጫ ፈተናን አስመልክቶ ነቀምቴ የሚገኘው ዋና ግቢ ተማሪዎች ባለፈው ሣምንት ትምህርት አቁመው እንደነበረና ቅዳሜ ይመለሳሉ ተብሎ ሲጠበቅ እንዳልተመለሱ፤ የሻምቡ ግቢ ተማሪዎችም ተመሣሣይ ጥያቄ ትናንት (ሰኞ) አንስተው በሰላም መለያየታቸውን ገልፀዋል።

በተማሪዎቹ መካከል ግጭቱ እኩለ ሌሊት ላይ መነሳቱንና ከተንቤን የመጡ ናቸው ከተባሉት ተማሪዎች አንደኛው በድብደባ ሲሞት የሁለተኛው ግን እየተጣራ መሆኑን ዲኑ አመልክተው እርሣቸው በግቢው ውስጥ በኃላፊነት ባገለገሉባቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ እንዲህ ጎሣ የለየ ጥቃት ሲፈፀም ሲያዩ የትናንት ሌሊቱ የመጀመሪያቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

Your browser doesn’t support HTML5

ሻምቡ ውስጥ የሁለት የትግራይ ተማሪዎች ሕይወት ጠፋ