ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ኒው ዮርክ ታይምስ አደባባይ የተሰበሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የፈረንጆቹን አዲስ አመት በፌሽታ ተቀብለውታል። በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ ግጭቶች እና የፀጥታ ስጋቶች ክብረ-በዓሉን ቢያደበዝዙት በአደባባዩ ላይ የወረደው አንፀባራቂ ኳስ እ.አ.አ የሚከበረው የ2024 አዲስ አመት በተሰፋ መጀመሩን አመላክቷል።
በሰዓት አቆጣጠር ልዩነት ምክንያት እኩለ ለሊት ላይ አዲስ አመት መግባቱን በመጀመሪያ ያወጀችው አውስትራሊያ ስትሆን፣ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች በዋና ከተማዋ ሲድኒ ከሚገኘው ታዋቂ የኦፔራ ማሳያ ስፍራ የተካሄደውን የርችት ስነስርዓት ተከታትለዋል። እንደ ኒው ዮርክ ያሉ ከተሞች ከ16 ሰዓታት በኃላ አዲሱን አመት ተቀብለዋል።
በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች አዲሱ አመት ከሀዘን ይልቅ ደስታን እንዲያመጣ በመመኘት በደስታ ሲቀበሉ የሚያሳዩ የተለያዩ ምስሎችም ይፋ ተደርገዋል።
በእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ምክንያት በኒው ዮርክ በእየለቱ የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ በመቆየታቸው፣ በኒው ዮርክ የነበረውን የአዲስ አመት ክብረ-በዓል ፀጥታ ለማስከበር በሺዎች የሚቆጠሩ የፖሊስ አባላትን ያካተተ አነስተኛ ጦር ተሰማርቶ ነበር።
በፈረንሳይም ከ90 ሺህ በላይ ፖሊሶች እና የፀጥታ አባላት፣ በተለያየ አቅጣጫ የሚንፀባረቀውን የብርሃን ትዕይንት ለማየት በርካታ ህዝብ የተሰበሰበበትን የሻንዘሊዜ መንገድ ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎችን ሲጠብቁ ታይተዋል።
በግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ በሚገኘው አስደናቂ እና ጥንታዊ የግሪክ ሀውልቶች ስብስብ ላይ፣ ዱባይ ውስጥ በሚገኘው ቡርጅ ካሊፋ የተሰኘ የዓለማችን ሰማይ ጠቀስ ህንፃ ላይ እንዲሁም በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የተካሄዱ አስደናቂ የርችት ስነስርዓቶችም የአዲሱን አመት አከባበር በደስታ የሞሉ ትዕይንቶች ነበሩ።
በአንፃሩ በቻይና ዋና ዋና ከተሞች ከደህንነት እና ከብክለስት ስጋት ጋር በተያያዘ ርችቶች በመከልከላቸው የአዲሱ አመት አቀባበል ቀዝቀዝ ያለ ቢሆንም፣ በርካታ ሰዎች አደባባይ ላይ ተሰብስበው በተዋቡ አልባሳት የዳንስ ትዕይንቶችን አሳይተዋል። በቻንግቺንግ ከተማም ፊኛዎች ተለቀዋል። የቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ለህዝባቸው ባደረጉት የአዲስ አመት ንግግር፣ ሀገራቸው በ2024 በኢኮኖሚ ማገገሚያ ግንባታዎች ላይ እንደምታተኩር ገልፀው፣ ቻይና "በእርግጠኝነት ከታይዋን ጋር ትዋሃዳለች" ሲሉም ቃል ገብተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በዩክሬን የምታካሂደው ወታደራዊ እንቅስቃሴ የአዲሱን አመት አከባበር ጥላ አጥልቶበታል። በሞስኮ ቀይ አደባባይ የተለመደው ርችት እና ኮንሰርት የተሰረዘ ቢሆንም ጥቂት ሰዎች አደባባዩ ላይ ተሰብስበው አዲሱን አመት ተቀብለዋል።